የአየር ጠባይ ስጋቶችን ለመቋቋም የሚቲዎሮሎጂ መረጃን መሠረት ያደረገ ቅድመ ዝግጅት ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
የአየር ጠባይ ስጋቶችን ለመቋቋም የሚቲዎሮሎጂ መረጃን መሠረት ያደረገ ቅድመ ዝግጅት ያስፈልጋል
አዳማ፤ ግንቦት 7/2018 (ኢዜአ)፦ የአየር ጠባይ ስጋቶችን ለመቋቋም በሚቲዎሮሎጂ የትንበያ መረጃ መሠረት ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የ2018 የበልግ ወቅት የአየር ጠባይ ትንበያ ግምገማና የመጪው የክረምት ወቅት የአየር ጠባይ አዝማሚያ ትንበያ ይፋ ለማድረግ ያዘጋጀው የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚና የማህበረሰቡ ኑሮ ከወቅታዊ የአየር ጠባይ ሁኔታ ጋር በቀጥታ የተቆራኘ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም እንደ በልግ እና ክረምት ያሉ ወቅቶች ለግብርና ምርታማነት፣ ለውኃ ሀብትና ለኢነርጂ አቅርቦት ያላቸው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህ ረገድ ኢንስቲትዩቱ ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚ እና ለሕብረተሰቡ የሚውሉ የሚቲዎሮሎጂ ትንበያና የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ አገልግሎቶችን በወቅቱና በብቃት የማሰራጨት ተግባር እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የዛሬው መድረክ የመጪውን የክረምት ወቅት ትንበያ ይፋ የሚደረግበት በመሆኑ፤ ለአርሶና አርብቶ አደሩ፣ ለውኃ ሀብት አስተዳደር ተቋማት፣ ለአደጋ ስጋት ሥራ አመራርና ለሌሎችም የልማት ዘርፎች ቀድሞ ለመዘጋጀት እጅግ ወሳኝ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የአየር ጠባይ ስጋቶችን ለመቋቋም የሚቲዎሮሎጂ መረጃን መሠረት ያደረገ ቅድመ ዝግጅት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዘበዋል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸው፤ ተቋሙ የአየር ጠባይ ለውጥን ለመቋቋም፣ የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስና አስቀድሞ በመተንበይ የደንበኞችንና የባለድርሻ አካላትን ፍላጎት ለማርካት በትጋት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለዚህም ከዋናው መሥሪያ ቤት ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ 11 የክልል የሚቲዎሮሎጂ ማዕከላትን በማደራጀት መረጃን በቅርበት ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢንስቲትዩቱ ዕለታዊ የአየር ሁኔታ ትንበያ ከመስጠት ባለፈ፤ የረጅም ጊዜ የአየር ጠባይ ትንበያን በመተንተንና በመገምገም ለተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የቅድመ ማስጠንቀቂያ አገልግሎት በወቅቱና በብቃት ለማሰራጨት እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል።
ይህም መረጃ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ በተለይም ለግብርና እና ለውኃ ዘርፍ የሚሰጠው ፋይዳ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።