የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ሥራ ላይ በማዋል ተጨባጭ ውጤቶች እየተገኙ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ሥራ ላይ በማዋል ተጨባጭ ውጤቶች እየተገኙ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2018 (ኢዜአ)፦ዓለም አቀፍ ስታንዳርድ የጠበቀ የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ሥራ ላይ በማዋል ተጨባጭ ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እና የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ፕሬዚዳንት አቶ ፈጠነ ተሾመ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢንስቲትዩቱ የትንበያ አቅም በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ዝርጋታና በተደራሽነት ረገድ ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገረ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅትም የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የአየር ሁኔታ ትንበያዎችን ለውሳኔ ሰጪ አካላትና ለተጠቃሚው ማኅበረሰብ በወቅቱ ተደራሽ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ለመስጠት ካስቀመጠው ግብ አንጻር፣ ግቡን ለማሳካት የሚያስችሉ ሁለንተናዊ የሚቲዎሮሎጂ ምልከታ መሠረተ ልማቶች በአገር አቀፍ ደረጃ መዘርጋታቸውን ጠቁመዋል።
የአየር ሁኔታን በቅርበት ለመከታተል የሚያስችሉ ዘመናዊ ራዳሮች በአራት ስትራቴጂካዊ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ተተክለው በቅርቡ ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ራዳሮቹ የተተከሉባቸው ቀጠናዎች በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በመካከለኛው ኢትዮጵያ እና በደቡብ ኢትዮጵያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህ ዘመናዊ ራዳሮች በተተከሉበት ስፍራ ዙሪያ እስከ 250 ኪሎ ሜትር ክብ ርቀት (ራዲየስ) ውስጥ ያለውን ማንኛውንም የሚቲዎሮሎጂ ለውጥና መረጃ በቀጥታ ወደ ማዕከላዊ የመረጃ ቋት የመላክ ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው አብራርተዋል።
ከራዳር ዝርጋታው በተጨማሪ፣ የአየር ንብረት መረጃዎችን በከፍተኛ ፍጥነት ወደ መረጃ ቋት የመላክ አቅም ያላቸው የ‘አውቶማቲክ ዌዘር ስቴሽኖች’ ተከላ እየተካሄደ መሆኑን አንስተዋል።
እነዚህ ወደ ሥራ የገቡና እየተዘረጉ ያሉ ቴክኖሎጂዎች ዓለም የደረሰበትን ከፍተኛ የሚቲዎሮሎጂ ምልከታ ደረጃ የጠበቁ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም የአገሪቱን የትንበያና የቅድመ ማስጠንቀቂያ አቅም በማጎልበት ረገድ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ቴክኖሎጂዎቹ ተደራሽነትን ከማስፋታቸውም በላይ ማኅበረሰቡ ወቅቱን የጠበቀና አስተማማኝ አገልግሎት እንዲያገኝ እንደሚያስችሉ አስገንዝበዋል።
የቴክኖሎጂ ውጤቶቹ ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ሊከሰት የሚችለውን ጉዳት በቅድመ ማስጠንቀቂያ ለመቀነስ ብሎም ለሌሎች መሠረታዊ ጉዳየች ያላቸው ፋይዳ የጎላ ነው፡፡