የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለዓለም አቀፍና ዳያስፖራ ማህበረሰብ የማስገንዝብ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለዓለም አቀፍና ዳያስፖራ ማህበረሰብ የማስገንዝብ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ፍትሐዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለዓለም አቀፍና ዳያስፖራ ማህበረሰብ የማስገንዝብ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን በዚምባቡዌ፣ ዛምቢያና ሞሪሽየስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደርና የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) የኢትዮጵያ ቋሚ ተጠሪ ረሽድ መሀመድ ገለጹ።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራና ኮሪደር ልማት ውጤታማ ሥራዎች በዲፕሎማሲ መስክ የሀገርን ስምና ገፅታ እያጎሉ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
አምባሳደር ረሽድ መሀመድ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ በኢ-ፍትሐዊ በደል ከታሪካዊ፣ መልክዓምድራዊና ሕጋዊ የባሕር በር ባለቤትነቷ እንድትነጠል መደረጉን አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው ካለው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና ካላት የህዝብ ቁጥር አንጻር በባለቤትነት የምታስተዳድረው፣ የወጪና ገቢ ንግዷን የሚያሳልጥላት አስተማማኝ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት አንስተዋል።
በመልክ-ዓምድራዊ አቀማመጥም ከቀይ ባሕር በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ እንደመሆኗ ከባሕር በር ባለቤትነት ተነጥላ ልትኖር እንደማይቻላት አስገንዝበዋል።
ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት የባሕር በር ባለቤት የነበረች መሆኗም የባሕር በር ባለቤትነቷን ሕጋዊና ምክንያታዊነት እንደሚያጎላው አብራርተዋል።
በዚህም የኢትዮጵያን ታሪካዊ፣ ሕጋዊ፣ መልክዓ-ምድራዊና ፍትሐዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ በተለይም ለዚምባቡዌ፣ ዛምቢያ፣ ሞሪሽየስና ኮሜሳ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ የማስገንዘብ ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ አድናቆትና ዕውቅና እየተቸረው እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በአረንጓዴ አሻራ የተመዘገበውን ስኬት በአፍሪካ ሀገራት ለማስፋት የዲፕሎማቲክ ግሪን ሌጋሲ ፎረም በመመስረት እየተሰራበት መሆኑን ተናግረዋል።
በኤምባሲው አስተባባሪነትም በዚምባቡዌ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እየተካሄደ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር የዲፕሎማሲ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝም አምባሳደሩ ጨምረው ገልጸዋል።
ለአብነትም በቅርቡ የኢትዮጵያና ዚምባቡዌ የጋራ ሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ በማካሄድ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ይበልጥ የሚያጠናክሩ ስምምነቶችን ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በዛምቢያ በክብር ቆንፅላ እንድትወከል የሚያስችሉ ሥራዎችን በማከናወን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።