ከሀገር የወጡ ቅርሶችን የማስመለስ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
ከሀገር የወጡ ቅርሶችን የማስመለስ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2018 (ኢዜአ)፦በተለያዩ ጊዜያት ከሀገራቸው የወጡ ቅርሶችን የማስመለስ ጥረቶች ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ገለጹ።
ዋና ዳይሬክተሩ ይህንን የገለጹት በተለያዩ ጊዜያት ከሀገር ወጥተው የነበሩ ታሪካዊ ቅርሶች ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ርክክብ በተደረገበት ወቅት ነው።
በኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን በተካሄደው በዚህ የቅርሶች ርክክብ መርሃ-ግብር ላይ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፣ የመከላከያ ሙዚየም እና ቅርስ ጥናት አስተዳደር ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ጥሩዬ አሰፌ፣ አባት አርበኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች ተገኝተዋል።
ቅርሶቹን የእንግሊዝ ንጉስ የቤተሰብ ሙዚየም (King’s Own Royal Regiment Museum) ኃላፊ ኮሎኔል ሮቢን ጃክሰን (ዶ/ር) እና የማህበራዊ አንትሮፖሎጂስት፣ ተመራማሪና የኢትዮጵያ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባል የሆኑት አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው አስረክበዋል።
ከቅርሶቹ መካከልም ከእንግሊዝ ሀገር ለረጅም ጊዜ ቆይታ በኋላ ወደ ሀገራቸው የተመለሱት የአፄ ቴዎድሮስ የእጃቸው የወርቅ አምባር፣ የጸጉራቸው ቁንዳላ (ትንሽ ዘለላ) እና የሸማ ሸሚዝ ቁራጭ ይገኙበታል፡፡
እንዲሁም የአጼ ቴዎድሮስ ባለቤት የነበሩት የእቴጌ ጥሩወርቅ ውቤ የጸጉር ጌጥ (ወለባ)፣ ታሪካዊ ጋሻ፣ የመጠጫ ዋንጫዎች እና የተለያዩ ስዕሎች ተካተዋል፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ እለቱ ለመላው ኢትዮጵያውያን ትልቅ ቀን መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መቅደላ በርካታ ቅርሶች የተዘረፉበት ቦታ መሆኑን ያመለከቱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የአጼ ቴዎድሮስ ቁንዳላም በዚሁ ስፍራ ተቆርጦ መወሰዱን አስታውሰዋል።
እነዚህን ቅርሶች ለማስመለስ በተደረጉ ተከታታይ ውይይቶችና በተደረሰው ስምምነት መሰረት ቅርሶቹ ወደ ሀገራቸው ሊመለሱ መቻላቸውን ገልጸው፣ በዛሬው እለት የተረከቧቸው ቅርሶች በቀጣይ ለህዝብ እይታ እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል።
የማህበራዊ አንትሮፖሎጂስትና የቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባል አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ እለቱ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ቀን መሆኑን ገልጸው የተመለሱት ቅርሶች ይዘትና ታሪካዊ እውነታ በጥልቅ ምርምር የተረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቅርሶቹ ታሪክን ህያው የሚያደርጉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ አሁንም በቀጣይ ሌሎች ቅርሶችን ለማስመለስ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የእንግሊዝ ንጉስ የቤተሰብ ሙዚየም ኃላፊ ኮሎኔል ሮቢን ጃክሰን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ እነዚህ ቅርሶች ለኢትዮጵያውያን ያላቸው ፋይዳ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የቅርሶቹ በሰላም መመለስ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን መልካም ወዳጅነት በተግባር የሚያሳይ መሆኑንም ተናግረዋል።