ቀጥታ፡

በዞኑ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 700 ሺህ ሔክታር መሬት በተለያዩ ችግኞች ለመሸፈን ዝግጅት ተደርጓል

ገንዳውኃ፤ ግንቦት 7/2018 (ኢዜአ)፦በምዕራብ ጎንደር ዞን በመጪው ክረምት በሚካሔደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በ700 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የተለያዩ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉን  የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡

​በመምሪያው የደን ባለሙያ አቶ ጋሻው ታያቸው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በመጪው ክረምት ወቅት በሚካሔደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሀገር በቀል የሆኑ የደን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው። 

ለዚህም ከአንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን በላይ ችግኞች ​የተዘጋጁ ሲሆን የችግኞቹ ዝርያ በአካባቢው ያለውን ሞቃታማ የአየር ፀባይና ስነ- ምህዳር የተላመዱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።


 

ችግኞቹን ለመትከልም እስከ አሁን ከ80 ሺህ በላይ ጉድጓዶች ተቆፍረው የተዘጋጁ ሲሆን፤ ሽመል ፣ አካሻ ሰኔጋል ፣ ኒም ፣ ዋንዛና ሌሎች ዝርያዎችም እንደሚገኙበት ነው ያስረዱት።

​በዞኑ የመተማ ወረዳ ኩመር አፍጥጥ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መኮንን ውቤ እንዳሉት፣ በአካባቢያቸው የነበሩ ግዙፍ ዛፎች በመመንጠራቸው የዝናብ መዛባትና የሙቀት መጨመር ሲያጋጥም ቆይቷል።

ይህንን ችግር በመሰረታዊነት ለመቅረፍም ሀገር በቀል ችግኞችን በማፍላት ነባር ደኖችን ለመተካት እየተሰራ ያለው ስራ የሚያስደስት ነው ሲሉ ገልፀዋል።


 

ችግኞቹ ድርቅን የመቋቋም አቅማቸው ከፍተኛ በመሆኑ በወቅቱ በመትከልና በመንከባከብ የጽድቀት መጠኑን ለመጨመር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

አርሶ አደር ስመኘው አዱኛ በበኩላቸው፤ የተዘጋጁት ሀገር በቀል ችግኞች ለአፈር ለምነትና ለከብቶቻቸው መኖ ጠቃሚ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የግብርና ባለሙያዎች የሚሰጡንን ምክር በመከተል በችግኝ ተከላው ላይ በግንባር ቀደምነት ለመሳተፍ ተዘጋጅተናል ሲሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም