ቀጥታ፡

በክልሉ የአፈር ማዳበሪያ ከአካባቢው የአፈር ሁኔታ ጋር በማስማማት መቅረብ መጀመሩ በምርት ላይ ውጤት እያስገኘ ነው

ሰመራ፤ ግንቦት 7/2018 (ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል የአፈር ማዳበሪያን ከአካባቢው የአፈር ሁኔታ ጋር በማስማማት መቅረብ መጀመሩ በምርት ላይ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ገለፀ።

ለዘመናት በከብት እርባታ የሚታወቀው የአፋር ህዝብ፣ ከለውጡ ዓመታት ወዲህ ወደ መስኖና ቋሚ ግብርና በስፋት እየተሸጋገረ ይገኛል። 

የአፈር ለምነትን ለማሻሻልና የግብርና ስራውን የባህላዊ አሰራር ተጽዕኖ በማውጣት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም በክልሉ እየተለመደ መጥቷል። 

በክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የእርሻ ኢንቨስትመንትና ግብአት ዘርፍ ምክትል ኀላፊ አቶ ሃሩን ዓሊ እንደተናገሩት፤ የአፈር ማዳበሪያውን ከአካባቢው የአፈር ሁኔታ ጋር በማስማማት ማቅረብ መጀመሩ ምርትን በማሳደግ ላይ ትልቅ መሻሻል አሳይቷል።

በበጀት ዓመቱ 50 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማስገባት ታቅዶ ወደ ስራ የተገባ ሲሆን በእስካሁኑ እንቅስቃሴ 48 ሺህ 800 ኩንታል ቀርቦ በጋሊኮማና ደንከሊያ ዮኒየኖች አማካኝነት በመሠራጨት ላይ መሆኑም ተመላክቷል።

በክልሉ የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም በይፋ መጀመሩን ተከትሎ፣ በተለያዩ የአዝዕርት፣ የፍራፍሬና የአትክልት ምርቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ የምርት ጭማሪ መታየቱን ገልጸዋል። 

ይህ ስኬትም ባለፉት የለውጥ ዓመታት በዘርፉ የተከናወኑ የለውጥ ስራዎችና የተመዘገቡ መሻሻሎች ውጤት መሆኑን ገልጸዋል። 

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በአፋር ክልል የተከናወኑ የግብርና ስራዎች፣ በረሃማ አካባቢዎችን ማልማት እንደማይቻል ይታመንበት የነበረውን የተዛባ ትርክት የቀየሩና ማንኛውንም ሰብል ማምረት እንደሚቻል በተግባር ያረጋገጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የግብዓት አቅርቦቱ ብቻውን ስኬታማ ሊሆን እንደማይችል የጠቀሱት አቶ ሃሩን፣ ማዳበሪያው በአግባቡና በሳይንሳዊ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል የእያንዳንዱ አርሶ አደር ማሳ በባለሙያዎች እንዲታገዝ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል። 

ይህም አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ከቴክኖሎጂው ተገቢውን ውጤት እንዲያገኝና የምርት ብክነትን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም