ቀጥታ፡

በክልሉ ጥምር ጥቅም የሚሰጡ ችግኞችን በሳይንሳዊ መንገድ በመትከል የጽድቀት መጠናቸውን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል

አዳማ፤ ግንቦት 7/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ጥምር ጥቅም የሚሰጡ ችግኞችን በሳይንሳዊ መንገድ በመትከል የጽድቀት መጠናቸውን ለማሳደግ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ። 

በክልሉ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ችግኞች መዘጋጀታቸውም ተገልጿል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉና ጥምር ጥቅም የሚሰጡ ችግኞችን የጽድቀት መጠን ለማሳደግ፤ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶችን በተገቢው ሁኔታ በማዘጋጀት በቂ አየርና የአፈር እርጥበት እንዲያገኙ ማድረግ ተገቢ መሆኑ ተመላክቷል። 


 

በቦታ መረጣ ወቅት የውኃ እጥረት እንዳይኖር የውኃ ማጠራቀሚያ ገንዳዎችን መሥራትና ችግኞቹ ለአካባቢው የአየር ንብረት ተስማሚ መሆናቸውን ማረጋገጥ የትኩረቱ አካል ነው።

በተጨማሪም የችግኞች በሽታን የመቋቋም አቅም መኖር፣ ከተተከሉ በኋላ ከእንስሳት ንክኪ መከላከል እንዲሁም ቀጣይነት ያለው የክትትል ሥራ ማከናወን ለጽድቀታቸው ድርሻው የጎላ መሆኑ ተጠቁሟል።

የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የደን ልማትና ተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ዳይሬክተር ከተማ አብዲሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በለውጡ ዓመታት በክልሉ የተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተግባራት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በዘላቂነት በመቋቋም ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ እያገዙ ነው።

መርሃ ግብሩን ከአካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ጋር በማስተሳሰር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና የአካባቢውን ሥነ-ምህዳር ለመጠበቅ በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት መገኘቱንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። 


 

ይህንኑ ተግባር ለማስቀጠል ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለተለያዩ ጥቅሞች የሚውሉ ችግኞች መዘጋጀታቸውንና የተከላ ሂደቱ በሳይንሳዊ መንገድ እንዲከናወን ለአርሶ አደሩ ሥልጠና መሰጠቱን ጠቁመዋል።

በመጪው ክረምት ለተከላ ከተዘጋጁት ችግኞች መካከል ለደን፣ ለውበትና ለምግብነት የሚውሉ ፍራፍሬዎች እንደሚገኙበት ጠቁመው፤ ለዚህም የመሬት ልየታ፣ ካርታ የማዘጋጀትና የጉድጓድ ቁፋሮ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም