በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮ የምርት ዘመን ከ89 ሺህ ኩንታል በላይ የሻይ ምርት ለገበያ ቀርቧል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮ የምርት ዘመን ከ89 ሺህ ኩንታል በላይ የሻይ ምርት ለገበያ ቀርቧል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው የምርት ዘመን በ1 ሺህ 280 ሄክታር መሬት ላይ ከለማው ሻይ ከ89 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለገበያ መቅረቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የፍራፍሬ ልማት ዳይሬክተር አቶ ቻላቸው አዱኛ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ የሻይ ልማት ኢንሼቲቭ ተቀርጾ ወደ ሥራ ከተገባ ወዲህ የአርሶ አደሩ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መጥቷል።
የክልሉ መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት፣ የምርት ጥራትና ብዛትን የሚጨምሩ የተሻሻሉ የሻይ ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ እንዲቀርቡ ተደርጓል ብለዋል።
የሻይ ልማቱ በስፋት እየተከናወነ የሚገኘው የክልሉን ዞኖች መልክዓምድርና ተስማሚ የአየር ንብረት መሰረት አድርጎ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም በጅማ፣ ኢሉባቦር እና ቡኖ በደሌ ዞኖች ውስጥ መሆኑን ጠቁመዋል።
ልማቱን ይበልጥ ለማሳደግ የተሻሻሉ ዝርያዎች የሚባዙባቸው የሻይ ችግኝ ጣቢያዎች በመንግስትና በአርሶ አደሮች ደረጃ ተዘጋጅተው ወደ ሥራ ገብተዋል ብለዋል።
ባለፉት 9 ወራት ለገበያ የቀረበው ከ89 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ክልሉ በዘርፉ ያለውን እምቅ አቅም የሚያሳይ መሆኑን አቶ ቻላቸው ገልጸዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት አርሶ አደሮች በዘርፉ ወደ ኢንቨስትመንት እንዲሸጋገሩ በተደረገው ጥረት እስካሁን 10 አርሶ አደሮች ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገር መቻላቸውንም አስረድተዋል።
በቀጣይም ዘርፉን ይበልጥ ለማዘመን እና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሻይ ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ግንባታ ማፋጠን እና ለምርቱ አስተማማኝ የገበያ ትስስር መፍጠር ትኩረት የተሰጣቸው ተግባራት መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ይህ የሻይ ልማት እንቅስቃሴ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ፣ በባለሀብቶችና በአርሶ አደሮች መካከል ያለውን ቅንጅት በማጠናከር ረገድ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል።