በወላይታ ሶዶ ከተማ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ቅርንጫፍ መከፈቱ ተገልጋዮችን ከእንግልትና ወጪ ታድጓል - ኢዜአ አማርኛ
በወላይታ ሶዶ ከተማ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ቅርንጫፍ መከፈቱ ተገልጋዮችን ከእንግልትና ወጪ ታድጓል
ወላይታ ሶዶ፤ ግንቦት 7/2018 (ኢዜአ)፦የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የወላይታ ሶዶ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት መክፈቱ ፓስፖርት ለማውጣት ይገጥማቸው የነበረውን እንግልትና ወጪ እንዳስቀረላቸው ተገልጋዮች ገለጹ።
ተገልጋዮቹ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የጽህፈት ቤቱ ሥራ መጀመር ካላስፈላጊ ወጪና እንግልት ታድጓቸዋል። ቀደም ሲል ፓስፖርት ለማውጣት ወደ ሐዋሳ እና አዲስ አበባ ከተሞች ለመጓዝ ይገደዱ እንደነበር አስታውሰው፣ በዚህም ለተጨማሪ ወጪና ለገንዘብ ብክነት ይዳረጉ እንደነበር ገልጸዋል።
ቅርንጫፉ በከተማው ተከፍቶ በዲጂታል የታገዘ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ፣ ቀልጣፋ አሠራር እንዲኖር በማድረግ ጊዜና ድካም መቀነሱን ተናግረዋል።
ተገልጋዮቹ በቅርንጫፉ ቀልጣፋና ምቹ አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልጸው፣ የቅርንጫፉ መከፈት ፓስፖርት የማውጣቱን ሂደት በእጅጉ ማቅለሉን ተናግረዋል።
ፓስፖርት ማውጣት ፈልገው ነገር ግን ወጪና እንግልቱን በመፍራት ትተውት ለነበሩ በርካታ ነዋሪዎችም ትልቅ እፎይታ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ የኦንላይን አታችመንት ባለሙያ ጌታያውቃል ዮሐንስ እና የፓስፖርት ዕደላ ባለሙያ ሁለመናሽ ደቻሳ፤ ለተገልጋዮች ፈጣን አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በየቀኑ አገልግሎት ፈልገው የሚመጡ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ቢሆንም፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋይ እርካታን ለመፍጠር እየተጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሉቃስ ግርማ በበኩላቸው፤ ተቋሙ የመደበኛ ፓስፖርት አዲስ ማመልከቻ፣ የእድሳት እና የአስቸኳይ ምዝገባ አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በቀን ከ400 እስከ 600 የሚደርሱ ዜጎችን እያስተናገዱ መሆናቸውንና ባለፉት አራት ወራት ብቻ ከ9 ሺህ በላይ ፓስፖርቶችን ለማሰራጨት መቻሉን ገልጸዋል።
በኦንላይን ቅድመ ቀጠሮ ሥርዓት ረጅም ሰልፍን ማስቀረት ተችሏል ያሉት ኃላፊው፤ አገልግሎቱን ፈጣን፣ ግልጽ እና ተደራሽ ለማድረግ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ማንኛውም ዜጋ ተገልጋይ የልደት ካርድ፣ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ወይም የታደሰ የቀበሌ መታወቂያ በመያዝ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችልም አሳስበዋል።
አገልግሎቱን ይበልጥ ለማቀላጠፍ ከከተማውና ከዞኑ አስተዳደር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንም ኃላፊው አክለው ገልጸዋል።