በወራቤ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች የከተማዋን ገጽታ በመቀየር ለኑሮና ለቱሪዝም ተመራጭ እያደረጓት ነው - ኢዜአ አማርኛ
በወራቤ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች የከተማዋን ገጽታ በመቀየር ለኑሮና ለቱሪዝም ተመራጭ እያደረጓት ነው
ወራቤ፤ ግንቦት 7/2018 (ኢዜአ)፦በወራቤ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር፣ የወንዝ ዳርቻና የፓርክ ልማት ሥራዎች የከተማዋን ገጽታ በመቀየር ለኑሮና ለቱሪዝም ተመራጭ እያደረጓት መሆኑ ተገለጸ።
መንግስት ለከተሞች ልማት ትኩረት በመስጠት ተግባራዊ ያደረገው የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራ ከተሞችን ምቹ፣ ጽዱና ለኑሮ ተመራጭ እያደረጋቸው ነው።
ልማቱ በተቀናጀ መንገድ ተግባራዊ ከሆነባቸው ከተሞች አንዷ ወራቤ ስትሆን፣ ልማቱ የከተማዋን ድምቀት ከማጉላት ባለፈ ተወዳዳሪነቷን እያሳደገው መሆኑም ተገልጿል።
የወራቤ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሻፊ ሙዜ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በከተማዋ እየተተገበረ ያለው የኮሪደር፣ የወንዝ ዳርቻና የፓርክ ልማት ከተማዋን ጽዱና ለኑሮ ምቹ ከማድረግ ባለፈ ለቱሪዝም ያላትን ተመራጭነት እያሳደገው ነው።
የልማት ሥራው በከተማዋ ያሉ ጸጋዎችን ለይቶ ለልማት ለማዋል ማስቻሉን ጠቁመው፣ ለበርካታ የከተማዋ ነዋሪዎችም የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ልማቱ የመዝናኛ ስፍራ፣ የአደባባይ ኹነቶችን ማስተናገጃ ቦታ፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ምግብ ቤቶች፣ ሰው ሰራሽ ሐይቅና ሌሎች የኮሪደር ልማቶችን አካቶ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
እንደ ምክትል ከንቲባው ገለጻ በከተማው የኮሪደር ልማትን ጨምሮ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የህዝብ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ተጨባጭ ውጤት እያመጡ ነው።
የወንዝ ዳርቻ፣ የኮሪደርና የፓርክ ልማት ሥራዎችን በማጎልበት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ከተማዋን የሆቴልና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል ብለዋል።
የከተማዋ ነዋሪ ወጣት አብዲ ዋሴ በበኩሉ፤ በከተማው መንገድን ጨምሮ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች እየተከናወኑ መሆኑን ነው የገለጸው።
የልማት ሥራዎቹ ከተማዋን ምቹ፣ ማራኪና ተመራጭ ከማድረግ ባለፈ ወጣቱ ከአልባሌ ቦታ እንዲታቀብ እያገዙ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡
በወራቤ ከተማ እየተከናወነ ያለው የወንዝ ዳርቻ ልማት ለአካባቢው ነዋሪዎች ምቹ የመዝናኛ ስፍራ መፍጠሩን የተናገረችው ደግሞ ሌላኛዋ የከተማው ነዋሪ ወጣት አኒሳ ከድር ናት።
መዝናኛ ስፍራው ሠርግን ጨምሮ ሌሎች ማህበራዊ ኹነቶችን ማስተናገድ በሚያስችል መልኩ መገንባቱን ገልጻ፣ ልማቱን ለማስቀጠል የበኩሏን እንደምትወጣ አረጋግጣለች።