የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የማጠናቀቂያ ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የማጠናቀቂያ ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የ25ኛ ሳምንት መርሐ ግብር የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይደረጋሉ።
ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ልደታ ክፍለ ከተማ ከባህር ዳር ከተማ ይጫወታሉ።
ልደታ ክፍለ ከተማ በ22 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ባህር ዳር ከተማ በ19 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል።
በ26ኛ ሳምንት ወራጁን አርባምንጭ ከተማን 4 ለ 1 ያሸነፈው ልደታ ክፍለ ከተማ ዓመቱን በድል ለመቋጨት ይጫወታል።
በ26ኛ ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ 3 ለ 1 የተሸነፈው ባህር ዳር ከተማ ዓመቱን ድል ለማሳረግ ወደ ሜዳ ይገባል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ሲዳማ ቡና ከአርባምንጭ ከተማ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ሲዳማ ቡና በ35 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል። ወደ ሴቶች ከፍተኛ ሊግ መውረዱ የተረጋገጠው አርባምንጭ ከተማ በ10 ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃን ይዟል።
በ25ኛ ሳምንት ይርጋጨፌ ቡና ያለ ግብ አቻ የተለያየው ሲዳማ ቡና ዓመቱን በማሸነፍ ለመፈጸም ይጫወታል።
ከፕሪሚየር ሊጉ ለወረደው አርባምንጭ ከተማ ጨዋታው ከመርሐ ግብር ማሟያነት የዘለለ ትርጉም የለውም።
ሃዋሳ ከተማ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሃዋሳ ከተማ በ49 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው ቦሌ ክፍለ ከተማ በ43 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሁለቱ ቡድኖች ዓመቱን በድል ለማጠናቀቅ የሚያደርጉት ፍልሚያ ተመጣጣኝ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት እስከ ግንቦት 9 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ66 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በተመሳሳይ 66 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
የኢትዮ ኤሌክትሪኳ ዳግማዊት ሰሎሞን በ24 ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራች ይገኛል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ረድኤት አስረሳኸኝ ደግሞ በ20 ግቦች ተከታዩን ስፍራ ይዛለች።