የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅት
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከብሩንዲ ጋር ለሚያደርገው ሁለተኛ ዙር የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ የሁለተኛ ቀን ልምምዱን ዛሬ አድርጓል።
አሰልጣኝ ራውዳ ዓሊ ለ30 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ትናንት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ ዝግጅታቸውን የጀመሩ ሲሆን ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ሁሉም ተገኝተው ልምምዳቸውን አከናውነዋል።
በብሔራዊ ቡድኑ የሁለተኛ ቀን ዝግጅት ተጫዋቾች የእርስ በእርስ ጨዋታዎችን በማድረግ አቋማቸውን መፈተሻቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከብሩንዲ ጋር ግንቦት 16 የመጀመሪያ ጨዋታውን በሜዳው፣ የመልስ ጨዋታውን ግንቦት 23 ቡጁምቡራ ላይ ያከናውናል።
10ኛው የፊፋ የሴቶች ከ17 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ በጥቅምት ወር 2019 ዓ.ም በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።
በውድድሩ ላይ 24 ሀገራት ይሳተፋሉ። በዓለም ዋንጫው አፍሪካ ሞሮኮን ጨምሮ በአምስት ሀገራት ትወከላለች።
በማጣሪያ የሚያልፉ አራት የአፍሪካ ሀገራት በሶስት ዙሮች በሚደረጉ ጨዋታዎች ይለያሉ።