አንጋፋው የእግር ኳስ ሰው ጌታቸው ገብረማርያም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ - ኢዜአ አማርኛ
አንጋፋው የእግር ኳስ ሰው ጌታቸው ገብረማርያም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2018 (ኢዜአ)፦ የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች፣ ዓለም አቀፍ ዳኛ እና አመራር የነበሩት ጌታቸው ገብረማርያም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ጌታቸው ገብረማርያም በተጫዋችነት ለኦሜድላ እና ጥጥ ማኅበር እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫውተው ያሳለፉ ሲሆን በመቀጠል ለረጅም ዘመናት በዓለም አቀፍ ዳኝነት ጭምር በሚታወቁበት የዳኝነት ሙያ አገልግለዋል።
ከዳኝነት ከተገለሉ በኋላም በኮሚሽነርነት፣ በአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትነት እንዲሁም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች በጥቅሉ ከ60 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ በማገልገል ማሳለፋቸውን ፌዴሬሽኑ ገልጿል።
የአቶ ጌታቸው ገብረማርያም ሥርዓተ ቀብር ነገ በአማኑኤል ቤተ-ክርስቲያን ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይፈፀማል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአንጋፋው የእግር ኳስ ሰው ጌታቸው ገብረማርያም ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በመግለጽ ለቤተሰብ፣ ለወዳጅ ዘመድ፣ ለእግር ኳስ ቤተሰብ እና ለሙያ ባልደረቦች መፅናናትን ተመኝቷል።