ቀጥታ፡

አየር መንገዱ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በመግዛት፣ በማንቀሳቀስ እና በመጠገን ረገድ በአፍሪካ ግንባር ቀደም ነው  

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በመግዛት፣ በማንቀሳቀስና በመጠገን በአፍሪካ ቀዳሚ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

አየር መንገዱ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ዛሬ የመሬት ላይ አውሮፕላን ትዕይንት (Static Air Show) አካሂዷል። 

አውሮፕላኖች ለሕዝብ ዕይታ የሚቀርቡበትን ትዕይንት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ከፍተውታል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ለማክበር የተለያዩ መርሃ ግብሮችን በማከናወን ላይ ይገኛል። 

ዛሬ የቀረበው የመሬት ላይ አውሮፕላን ትዕይንትም የዚሁ ክብረ በዓል አካል መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ መርሃ ግብር አየር መንገዱ በየዓመቱ 21 ሚሊዮን መንገደኞችን እና 850 ሺህ ቶን ጭነት ለማጓጓዝ የሚጠቀምባቸውን ዘመናዊ አውሮፕላኖች ለማህበረሰቡ ያስተዋወቀበት መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሁል ጊዜም ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሆኑ አውሮፕላኖችን በመግዛት፣ በማንቀሳቀስ እና በመጠገን ረገድ በአፍሪካ ቀዳሚ መሆኑንም አረጋግጠዋል። 

ይህም አየር መንገዱን በአህጉሪቷ እጅግ ስኬታማ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃም ዘመናዊና አዳዲስ አውሮፕላን ስብስብ (Young Fleet) ያለው ተወዳዳሪ አየር መንገድ እንዳደረገው ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት አየር መንገዱ 147 አውሮፕላኖች እንዳሉት የገለጹት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ አሁን ላይ እያደገ ከመጣው ፍላጎት አኳያ ቁጥሩ በቂ አለመሆኑን አስረድተዋል። 

ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከቦይንግ እና ኤርባስ ኩባንያዎች ከ100 በላይ አውሮፕላኖች መታዘዛቸውን ጠቁመዋል።

አየር መንገዱ በአምስት አህጉራት፣ በ82 ሀገራት እና በ140 መዳረሻዎች በረራ በማድረግ ሰዎችን በማገናኘትና ባህላዊ ትስስር በመፍጠር ረገድ አስደናቂ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

አየር መንገዱ ላለፉት 80 ዓመታት ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በመጠቀም በአፍሪካ ሰማይ ላይ ቀዳሚ መሆኑን አመልክተው፤ ሀገራትን በማቀራረብና በዓለም አቀፍ የባህልና የንግድ ልውውጥ ረገድ ወሳኝ ሚና ሲጫወት መቆየቱን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም