ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የታሪክ፣ የፅናት፣ የሀገር ግንባታ ውጤትና የአፍሪካውያን የትስስር ተምሳሌት ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ አየር መንገድ የታሪክ፣ የፅናት፣ የሀገር ግንባታ ውጤትና የአፍሪካውያን የትስስር ተምሳሌት መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ የመሬት ላይ አውሮፕላን ትዕይንት (Static Air Show) መርሃ ግብር በአየር መንገዱ ቅጥር ግቢ አካሂዷል፡፡

እንዲሁም አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ የባህል ልውውጥ ወሳኝ ሚና እየተወጣ መሆኑን የሚያንፀባርቅ ዓለም አቀፍ የባህል ቀን በስካይ ላይት ሆቴል አክብሯል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከተመሰረተ ጥቂት ወራት በኋላ የተቋቋመ ታሪካዊ ተቋም ነው፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍና በአህጉር አቀፍ ደረጃ ህዝቦችን እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን የማሳለጥ ተልዕኮ ሰንቆ መነሳቱን አስታውሰዋል፡፡

አየር መንገዱ ባለፉት አስርት ዓመታት አፍሪካን ከቀረው ዓለም ጋር ድልድይ ሆኖ በማገናኘት መንገደኞችና ሸቀጦችን አጓጉዟል፤ ንግድና ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝምና ዲፕሎማሲ እንዲሳለጥ አድርጓል ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ቀዳሚ የአቪዬሽን ግሩፕ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ካሉ አየር መንገዶች አንዱ መሆን መቻሉንም ገልጸዋል፡፡

መንግስት ሁሉን አቀፍ ሪፎርም በማድረግ የዘርፉን መሰረተ ልማት በማዘመን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ የሀገራዊ ለውጥ አጀንዳ ማዕከል እንዲሆን አድርጓል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢኮኖሚ ስትራቴጂያዊ ምሰሶና የአፍሪካውያን የኩራት ምንጭ መሆኑን ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ በአቪዬሽንና ሎጂስቲክስ ያላትን መሪነት የሚያጠናክሩ ፖሊሲዎች ገቢራዊ እንደሚደረጉ ገልጸዋል፡፡

የአውሮፕላን ትዕይንቱ አየር መንገዱ ባለፉት ዓመታት ያስመዘገበውን የቴክኖሎጂ እድገትና የብቃት ጉዞ የሚያሳይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ለአካባቢ ጥበቃ ተስማሚ የአቪዬሽን፣ ዘመናዊ የሎጂስቲክስ ስርዓት እና በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስር ወደላቀ አህጉራዊ ውህደት ለመሸጋገር በትጋት እንሰራለን ብለዋል፡፡

ለአየር መንገዱ ስኬታማ ጉዞ አስተዋጽኦ ላደረጉ የቀድሞና የአሁኑ መሪዎች፣ ፓይለቶች፣ መሐንዲሶችና ለመላው ሰራተኞች ምስጋና አቅርበዋል።

አየር መንገዱ በአምስት አህጉራት፣ በ82 ሀገራት እና በ140 መዳረሻዎች በረራ በማድረግ ሰዎችን በማገናኘትና ባህላዊ ትስስር በመፍጠር ረገድ አስደናቂ ሚና እየተወጣ መሆኑ ይታወቃል።

አየር መንገዱ ላለፉት 80 ዓመታት ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በመጠቀም በአፍሪካ ሰማይ ላይ ቀዳሚ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም