ኢትዮጵያ በሕዝቦች መተባበር የጠነከረች፣ ልዩነትን ወደ ውበት የቀየረች፣ በኅብረ ብሔራዊ ቀለም የደመቀች መሆኗን ለዓለም ማሳየት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሕዝቦች መተባበር የጠነከረች፣ ልዩነትን ወደ ውበት የቀየረች፣ በኅብረ ብሔራዊ ቀለም የደመቀች መሆኗን ለዓለም ማሳየት ይገባል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሕዝቦች መተባበር የጠነከረች፣ ልዩነትን ወደ ውበት የቀየረች፣ በኅብረ ብሔራዊ ቀለም የደመቀች መሆኗን ለዓለም ማሳየት እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ ገለጹ፡፡
ዛሬ የተጀመረውና እስከ ግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆየው ሀገር አቀፍ የባህል እና ቋንቋ ሳምንት "የባህል ልማት ለኅብረብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ኃሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በመርሐ ግብሩ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቅሰሙ ማሞ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ተሳታፊዎች ታድመዋል፡፡
የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቅሰሙ ማሞ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያውያን የብዝሃ ማንነትና ባህል ባለቤት፣ ለዘመናት በአብሮነት የኖሩ ሕዝቦች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያውያን በርካታ ታሪካዊና ወቅታዊ ፈተናዎችን በጋራ ተሻግረው ለሀገር ግንባታ ትልቅ ድርሻ ማበርከታቸውን ገልጸው፤ ብዝሃ ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓላት በሕዝቦች መካከል አንድነት እና ትስስር እንዲጠናከር አስችለዋል ብለዋል፡፡
ባህል የትውልድ ማንነት መገለጫ ብቻ ሳይሆን የልማት፣ የሰላምና የዲፕሎማሲ ኃይል ነው ያሉት ሰብሳቢዋ፤ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን እምቅ የባህል፣ የቋንቋ፣ ቅርስና ሀገር በቀል ዕውቀት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ኢትዮጵያ የሰው ልጆች መገኛ፣ የጥንታዊ ባህልና የስልጣኔ መነሻ መሆኗን ታሳቢ በማድረግ ለዓለም ለማስተዋወቅ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
ሀገር አቀፍ የባህል እና ቋንቋ ሳምንቱ የኢትዮጵያ የባህል ትርኢት ከማሳየት ባለፈ በሕዝቦች መካከል ትስስርን በመገንባት የጋራ እሴቶችን ለወጣቱ ትውልድ የሚያስተላልፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ በሕዝቦች መተባበር የጠነከረች፣ ልዩነትን ወደ ውበት የቀየረች፣ በሕብረብሔራዊ ቀለም የደመቀች ሀገር መሆኗን ለዓለም የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
የሕዝቡን መልካም እሴቶች በመጠበቅ ለትውልድ ለማስተላለፍና ለማበልጸግ በጋራ መቆም ይገባል ያሉት ሰብሳቢዋ፤ ሁሉም ለሰላም፣ ለአንድነትና ለባህል ልማት በጋራ መስራት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡