የኢትዮጵያዊያን ባህላዊ ዕሴቶች የእርስ በእርስ መስተጋብርን በማጠናከር ለሀገር ዘላቂ ልማት ጉልህ ፋይዳ እያበረከቱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያዊያን ባህላዊ ዕሴቶች የእርስ በእርስ መስተጋብርን በማጠናከር ለሀገር ዘላቂ ልማት ጉልህ ፋይዳ እያበረከቱ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያዊያን በሕብር ያሸበረቁ ባህላዊ ዕሴቶች የእርስ በእርስ መስተጋብርን በማጠናከር ለሀገር ዘላቂ ልማት ጉልህ ፋይዳ እያበረከቱ እንደሚገኙ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ''የባህል ልማት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት'' በሚል መሪ ሃሳብ ከዛሬ ግንቦት 6 እስከ 10/2018 ዓ.ም የሚቆይ ሀገር አቀፍ የባህልና ቋንቋ ሳምንት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በባህል ሳምንቱ መክፈቻ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ ተጋባዥ እንግዶችና የባህል ሳምንት ተሳታፊዎች ታድመዋል።
በዚሁ ወቅት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ እንዳሉት፤ የባህል ሳምንቱ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር የህዝብ ለህዝብ የባህል ትስስርና ትውውቅን ለማጠናከር ታልሞ የተዘጋጀ ነው።
በባህልና ቋንቋ ሳምንቱም የባህላዊ አልባሳት፣ ምግቦች፣ የዕደ ጥበብ ውጤቶች፣ የባህል መገለጫዎችና ዕሴቶች ለህዝብ ዕይታ ክፍት መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በብዝኅነት ያሸበረቁ ውብ ባህላዊ ዕሴትና መገለጫዎች ባለቤት ናት ያሉት ሚኒስትሯ፤ የህዝብን ባህልና ቋንቋ በማልማት ለህዝብ አብሮነት እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ባህሎች የህዝብ አብሮነት፣ አንድነትና የጋራ መግባባት መሠረቶች መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያዊያን ዕሴቶችም የእርስ በዕርስ መስተጋብርን በማጠናከር ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት ጉልህ ፋይዳ እያበረከቱ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የህዝብን በብዝኅነት ያሸበረቁ ኅብረ ብሔራዊ ዕሴቶች በፖሊሲ የተደገፈ ልማት በማካሄድ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
የባህልና ቋንቋ ሳምንቱም የኢትዮጵያን ቱባ ባህላዊ ዕሴቶች ሳይበረዙና ሳይከለሱ ለትውልድ ለማስተላለፍ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አንስተዋል።
የህዝቦች አብሮነትና ትስስር ይበልጥ እንዲጠናከር እንዲሁም የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሚደረገው ጉዞም የባህል ልማት ወሳኝና የማይተካ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አብራርተዋል።
የዜጎች የባህላዊ ዕሴቶችም የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ በማነቃቃት ከፍተኛ አቅም እየፈጠረ እንደሚገኝ አንስተዋል።
የተለያዩ ባህሎችን ለቱሪዝም ልማት በማዋል የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆኑም ዘርፉን በዘላቂነት መደገፍ የሚያስችሉ የባህል መሠረተ ልማቶች እየተካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።