መቻል ወደ ሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና የተጠጋበትን ወሳኝ ድል አስመዘገበ - ኢዜአ አማርኛ
መቻል ወደ ሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና የተጠጋበትን ወሳኝ ድል አስመዘገበ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ32ኛ ሳምንት ተጠባቂ መርሐ ግብር መቻል ነገሌ አርሲን 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል።
ማምሻውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ቸርነት ጉግሳ፣ በረከት ደስታ፣ ዩጋንዳዊው ቻርልስ ሙሲጌ እና ፈቱዲን ጀማል (በፍጹም ቅጣት ምት) ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው መቻል በ52 ነጥብ ደረጃውን ከሶስተኛ ወደ ሁለተኛ ከፍ አድርጓል።
መቻል ከመሪው ሲዳማ ቡና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት በማጥበብ የዋንጫ ተፎካካሪነቱን አጠናክሯል። በውድድር ዓመቱም 13ኛ ድሉን አስመዝግቧል።
ከተከታታይ ድሎች በኋላ ሽንፈት ያስተናገደው ነገሌ አርሲ በ51 ነጥብ ከሁለተኛ ደረጃ ወደ ሶስተኛ ዝቅ ብሏል። በሊጉም ሰባተኛ ሽንፈቱን አስተናግዷል። በዋንጫ ፉክክሩም ወሳኝ ሶስት ነጥብ ጥሏል።
ዛሬ በተደረጉ የ32ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ሀዲያ ሆሳዕና የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡናን፣ ምድረ ገነት ሽሬ ኢትዮጵያ ቡናን በተመሳሳይ 1 ለ 0 አሸንፈዋል።
ወላይታ ድቻ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።