ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የቡና ላኪነት ሚና ይበልጥ ለማሳደግ ትኩረት ሰጥታለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የቡና ላኪነት ሚና ይበልጥ ለማሳደግ ትኩረት ሰጥታለች
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የቡና ላኪነት ሚና ይበልጥ ለማሳደግ የሚያስችል ስትራቴጂ ተግባራዊ በማድረግ በትኩረት እየሰራች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ ገለጹ።
ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት የአፍሪካ ቡና ጉባኤን ለማስተናገድ የሚያስችላትን ስምምነት ከኢንተር-አፍሪካ የቡና ድርጅት (Inter-African Coffee Organization) ጋር ተፈራርማለች።
ስምምነቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ እና የኢንተር-አፍሪካ የቡና ድርጅት ዋና ጸሐፊ አምባሳደር ሰለሞን ሩቴጋ ፈርመውታል።
አምባሳደር ሀደራ በወቅቱ እንደገለጹት፤ አፍሪካ በቡና ምርት የታደለች አህጉር ብትሆንም ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም ሳታገኝ ቆይታለች።
ቡና ለኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ዕድገትን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወታቸውን የሚመሩበት ዋና የግብርና ምርት መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በቡና ዘርፍ ውጤታማ የሚያደርጓትን የተለያዩ ተግባራት በትኩረት እያከናወነች እንደሚገኝ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸው፤ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የቡና ላኪነት ሚና ለማሳደግ የሚያስችል ስትራቴጂን ተግባራዊ አድርጋ እየሠራች ነው ብለዋል።
በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን ምርታማነት ለማሳደግ፣ አቅማቸውን መገንባትና የቡና ጥራትን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ ከኢንተር-አፍሪካ የቡና ድርጅት ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም 25 ቡና አምራች የአፍሪካ ሀገራት የሚሳተፉበትን ይህንን ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ ኢትዮጵያ ሙሉ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።
የኢንተር-አፍሪካ የቡና ድርጅት ዋና ጸሐፊ አምባሳደር ሰለሞን ሩቴጋ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ይህንን ትልቅ የአፍሪካ የቡና ጉባኤ ለማስተናገድ በመስማማቷ ድርጅታቸው የተሰማውን ከፍተኛ ደስታ ገልጸዋል።
ዋና ጸሐፊው አክለውም፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት የቡና ተወዳዳሪነትና ያካበተችው ሰፊ ልምድ ጉባኤው ስኬታማ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ያላቸውን እምነት ገልጸው፤ ለዝግጅቱ መሳካት ድርጅታቸው አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በአፍሪካ ውስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ 25 ቡና አምራች ሀገራት በተለያዩ ጊዜያት በመገናኘት የቡና ምርትና ምርታማነትን በተመለከቱ አጀንዳዎችና በዘርፉ ላይ በሚስተዋሉ ተግዳሮቶች ዙሪያ በመምከር የመፍትሔ አቅጣጫ ሲያስቀምጡ ቆይተዋል።
ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት በቡና ዘርፍ ላይ የሚመክር ስብሰባ የምታስተናግድ መሆኗ ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝና ልምዷን ለሌሎች ሀገራት እንድታካፍል ትልቅ በር ይከፍታል ነው ያሉት።
በተጨማሪም አፍሪካውያን ነጻ የንግድ ቀጣናን ተጠቅመው እርስ በእርስ ቡና መገበያየት የሚችሉበትን ምቹ መድረክ እንደሚፈጥርም አመልክተዋል።
ዝግጅቱ የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ ከማነቃቃት ባለፈ የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ የቡና ዝርያዎችና ባህላዊ የቡና አፈላል ሥርዓት ለዓለም ይበልጥ ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር አስገንዝበዋል።