ቀጥታ፡

ከተረጂነት የመውጣት ጉዳይ ሀገራዊ ክብርና ሉአላዊነትን የማረጋገጥ ወሳኝ ሀገራዊ አጀንዳ ነው

ሀዋሳ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፡-ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት የመውጣት ጉዳይ የሀገርን ክብርና ሉአላዊነት የማረጋገጥ ወሳኝ አጀንዳ መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና በግብርና ሚኒስቴር ትብብር "ከተረጅነት ወደ ምርታማነት" በሚል መሪ ሃሳብ በሐዋሳ ከተማ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።


 

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በወቅቱ፤ የኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት በፅኑ መሰረት ላይ ማኖር የሚቻለው በምግብ ራስን በመቻል ከተረጅነት መውጣት ሲቻል መሆኑን ገልጸው ከተረጅነት የመውጣት ጥረት የብሄራዊ ጥቅምና የሉአላዊነት ጉዳይ ነው ብለዋል።

ከተረጂነት የመውጣት ጉዳይ የብሔራዊ ጥቅም አካል ሆኖ የመንግስት ስትራቴጂክ አጀንዳ ተደርጎ በፖሊሲ አቅጣጫ እየተመራ ይገኛል ነው ያሉት።

በመሆኑም ምርታማነትን በማሳደግ የሀገርን ብልጽግና እውን በማድረግ የኢትዮጵያን የድህነት ታሪክ የመቀየር ጉዳይ በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ይገኛል ብለዋል።

የሀገርን እምቅ ሃብቶች በማልማት የምርት አቅምን በማሳደግ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን በራስ አቅም የመመከት ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት አስጠብቆ ለመዝለቅ የተረጅነትና የልመና አስተሳሰብን በማስወገድ አልምቶና አምርቶ ብልጽግናዋን እውን ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የቤተሰብና የማህበረሰብ ብልፅግና ማረጋገጥና ሀገርን ከተረጅነትና ጥገኝነት ማላቀቅ የመንግስት የፖሊሲ አቅጣጫ ግቦች መካከል መሆኑንም ለአብነት ጠቅሰዋል።

ከድህነት በመውጣት የሚደረገውን ጥረትና እንደ ሀገር የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የሚደረገው ጥረት መቀጠሉን አንስተው በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር ) በበኩላቸው፤ የሀገርን እምቅ ጸጋዎች በማልማት ምርታማነትን በማሳደግ ከራስ የተሻገረ ስኬት ማስመዝገብ እንደሚቻል የተመዘገቡ ውጤቶች ማሳያ ናቸው ብለዋል።


 

በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች ባለፉት ጥቂት አመታት የመጡ ለውጦችና የተመዘገቡ ስኬቶች እምቅ አቅሞችን ወደ ተጨባጭ ውጤት መለወጥ ያስቻሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም በግብርናው ዘርፍ በተለያዩ ኢንሸቲቮች የተጀመሩ የልማት ጥረቶችን ዘላቂ በማድረግ ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት የመውጣት ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፤ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት መሻገር የሀገር ወሳኝ አጀንዳ መሆኑን አንስተው የኢትዮጵያን ተረጂነት ታሪክ የማድረግ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።


 

በተረጅነት ዙሪያ የዜጎች የአስተሳሰብ ለውጥ ወሳኝ መሆኑን አንስተው በዚህ ረገድ ሚዲያዎች የይዘት ስራዎችን በልዩ ትኩረት መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም