ቀጥታ፡

የማዕድን ትሩፋት ለኢትዮጵያ ትንሳኤ

ባለፉት የለውጥ ዓመታት መንግሥት የማዕድን ዘርፍን ከነበረበት መዋቅራዊ ችግር በማውጣት ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገትና ለብሔራዊ ሉዓላዊነት ምሰሶ እንዲሆን ለማድረግ ቆራጥ እርምጃዎችን ወስዷል።

ቀደም ሲል ዘርፉ ግልጽነት በጎደለው አሠራር፣ በሕገ-ወጥ ዝውውርና የጥቂቶች መጠቀሚያነት ተተብትቦ የቆየ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት "እርግማን" ወደ "ልማት መሣሪያነት" ተቀይሯል። በመደመር መንግሥት ዕይታ የማዕድን ዘርፍ ልማት ለኢትዮጵያ የሰላም፣ የዕድገትና የብሔራዊ ሉዓላዊነት ምንጭ እንዲሁም ለዘላቂ ልማትና ለኅብረተሰብ ተጠቃሚነት ወሳኝ ምሰሶ ሆኖ ያገለግላል። ዘርፉን የኢኮኖሚው ምሰሶ ለማድረግ በተወሰደው የሪፎርም እርምጃ፣ የማዕድን ሀብት አስተዳደር ሥርዓቱ በቴክኖሎጂ እንዲደገፍና ተጠያቂነት የሰፈነበት እንዲሆን በማድረግ የኮንትሮባንድ ንግድን በከፍተኛ ሁኔታ መግታት ተችሏል።

በተለይም ማዕድናትን በጥሬው የመላክ ልማድን በመቀየር፣ በሀገር ውስጥ የማዕድን ምርቶችን ዕሴት የሚጨምሩ ፋብሪካዎችንና የወርቅ ማጣሪያዎችን በመገንባት የውጭ ምንዛሬ ግኝታችን ወደ ላቀ ደረጃ ተሸጋግሯል። የወርቅ ወጪ ንግድን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት 2012 በጀት ዓመት 3.3 ቶን የነበረው ምርት 2017 በጀት ዓመት ወደ 38.83 ቶን አድጓል። ይህም ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ 200 ሚሊዮን ዶላር ወደ 3.46 ቢሊዮን ዶላር ከፍ እንዲል አድርጎታል። ይህ ውጤት የተገኘው የኮንትሮባንድ መንገዶችን በቴክኖሎጂ በታገዘ መዋቅር በመዝጋትና የገበያ ሥርዓቱን በማዘመን ነው።

በተጨማሪም ለኮንስትራክሽን ግብዓት የሚሆኑ እንደ ሲሚንቶ ያሉ ምርቶች በከፍተኛ ሁኔታ በአቅርቦት እንዲጨምሩ ተደርጓል። በአፍሪካ ግዙፍ የሆነውን የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካን ጨምሮ አዳዲስ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ በመግባታቸው፣ የሲሚንቶ ምርት 2014 ከነበረበት 6.2 ሚሊዮን ቶን 2017 ወደ 9.1 ሚሊዮን ቶን ደርሷል።

የሀገር ውስጥ ምርትን በመተካት ረገድም ትልቅ ስኬት ተመዝግቧል። ቀደም ሲል ለሲሚንቶ ምርት የሚያስፈልገው የድንጋይ ከሰል በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች ከውጭ ይገባ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት አራት የድንጋይ ከሰል ፋብሪካዎች ወደ ምርት ገብተው ምርቱን በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏል። በተመሳሳይ ለዓመታት የሕዝባችን ምኞት የነበረው የካሉብ ጋዝ ሀብት ለልማት እንዲውል የተደረገ ሲሆን፣ ይህም ለማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ፣ ለትራንስፖርትና ለኃይል አቅርቦት የሚውልበት ሥርዓት እየተዘረጋ ይገኛል። ማዕድን በሚወጣባቸው አካባቢዎች ያሉ ማኅበረሰቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም መንግሥት የሮያሊቲ ክፍያ እና ታክስን ግልጽ እና ፍትሐዊ በሆነ ቀመር እንዲያገኙ አድርጓል። ይህም የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረተ ልማቶች እንዲስፋፉና ባሕላዊ አምራቾች ወደ ተሻለ የሥራ ዘዴ እንዲሸጋገሩ ዕድል ፈጥሯል።

መንግሥት ዘርፉን ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን እንዲውል ግልጽ የፖሊሲ አቅጣጫ አስቀምጦ እየመራው ይገኛል። በአካባቢ ጥበቃ ረገድም ጠንካራ የቁጥጥር ዐቅምና የሕግ ማሕቀፍ በመገንባት ተፈጥሮን የመጠበቅ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል።

በሚቀጥሉት  ዓመታት ለሀገራችን ብልፅግና ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ባላቸው ማዕድናት ላይ ሰፊ ጥናትና ምርምር እንዲደረግ ትኩረት ይሰጣል። በተለይም በማዳበሪያ ፋብሪካ ላይ የተጀመረው ጥረት በፔትሮ-ኬሚካልና በተያያዥ ፕሮጀክቶች እንዲቀጥል ይደረጋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ የሆኑ እንደ ሊቲየም ያሉ ብርቅዬ ማዕድናት  ለሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገትና ለቴክኖሎጂ ፈጠራ እንዲውሉ በቁርጠኝነት ይሠራል። የማዕድን አካባቢዎች ሰላማዊ፣ የአካባቢውን ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉና በሕግ የሚመሩ እንዲሆኑ ይደረጋል።

እስካሁን በተከናወኑ  ሥራዎች የማዕድን ሀብታችን ለኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን አብነት እንዲሆን መሠረት ጥሏል። ይህ የተቀናጀ መሪነት ማዕድን ለኢትዮጵያ የሰላም፣ የዕድገትና የብሔራዊ ሉዓላዊነት ምንጭ እንዲሆን መሠረት ጥሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም