በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ከተረጅነት የመውጣት ጥረትን ለማሳካት የሚያስችል ተጨባጭ ውጤት እያመጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ከተረጅነት የመውጣት ጥረትን ለማሳካት የሚያስችል ተጨባጭ ውጤት እያመጡ ነው
ሀዋሳ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ከተረጅነት የመውጣት ጥረትን ለማሳካት የሚያስችል ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ ገለጹ።
"ከተረጅነት ወደ ምርታማነት" በሚል መሪ ሃሳብ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና በግብርና ሚኒስቴር ትብብር የተዘጋጀ የውይይት መድረክ በሐዋሳ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ፣ ሀገራዊ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት የመውጣት ጥረት ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በግብርና ልማት በተለይም የስንዴ ምርታማነትን በማሳደግ ከራስ አልፎ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የተመዘገበውን የላቀ ስኬት ለአብነት ጠቅሰዋል።
በሌሎች የተለያዩ የግብርና ልማት ስራዎችን በተጠናከረ መልኩ በማከናወን ምርታማነትን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
የሀገር በቀል የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ በማድረግ በሁሉም ሴክተሮች የተከናወኑ የልማት ስራዎችም ሀገራዊ እመርታና ማንሰራራት ማምጣት ያስቻሉ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም ሀገራዊ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት የመውጣት ጥረት ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ይገኛል ብለዋል።
በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ከተረጅነት የመውጣት ጥረትን ለማሳካት የሚያስችል ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዋና ስራ አስፈፃሚ ሠይፈ ደርቤ፤ በበኩላቸው እንደ ሀገር በምግብ ራስን ለመቻል የተጀመረው ግብ እንዲሳካ በቂ ግንዛቤ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
ለዚህም ሚዲያ የማይተካ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸው ኢዜአ ይህንን ሀገራዊ ትልም ለማሳካት የይዘት ስራዎችን በስፋት ተደራሽ የማድረግ ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የተያዘውን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት የሚደረገው ጥረት እንዲሳካ ኢዜአ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ እና የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎችም የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።