ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን ከተረጂነት ወደ አምራችነት ፤ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ጉዞ

የመደመር መንግስት የኢኮኖሚ እሳቤ የሀገራችንን ግብርና በተሟላ መልኩ ለማዘመን የሚያስችል ትልቅ ራዕይ ላይ የተመሠረተ ነው። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለዘመናት ከድህነት አዙሪት መውጣት ያልቻለው የምርት ሂደቱ ከዝናብ ጥገኝነት እና ከኋላቀር አሠራር ባለመላቀቁ እንደሆነ ይታመናል ።

የግብርናው ዘርፍ ማሻሻያ ዋና ግብ የዜጎችን ክብር ከፍ የሚያደርግና ሀገራዊ የምግብ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ እንዲሆን ተደርጓል። ለዚህም የገጠሩን ማኅበረሰብ ሕይወት ለመለወጥና ሀገራዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ኢንደስትሪያላይዜሽንና የግብርና ትራንስፎርሜሽን እንደ ዋና መሠረት ተቀምጠዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት መንግሥት የግብርናውን ኋላቀር ሂደት በመቀየር ቴክኖሎጂን እንደ ዋና ግብዓት በመጠቀም ረገድ ትልቅ የታሪክ እጥፋት ፈጥሯል። ይህም ግብርናው ከልመናና ከችሮታ ወጥቶ የኢኮኖሚው ዋና ሞተር እንዲሆን አስችሎታል። በተለይም አርሶ አደሩን ወደ ገበያ-ተኮር ምርት በማሸጋገር፣ የሥነ-ምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና ለሚሊዮኖች የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል። በኢኮኖሚ ማሻሻያው አማካኝነት ግብርናን የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ ግብዓት በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካትና ለውጭ ገበያ ጥራት ያለው ምርት ለማቅረብ ጠንካራ መሠረት ተጥሏል።

በመንግሥት የተቀናጀ ጥረት የተገኙ ውጤቶችም የሚያበረታቱ ናቸው። 2013 በጀት ዓመት 17.2 ሚሊዮን ሄክታር የነበረው የታረሰ መሬት፣ 2017 በጀት ዓመት ድግግሞሽን ጨምሮ ወደ 32.2 ሚሊዮን ሄክታር አድጓል። በዚህም ጠቅላላ የሰብል ምርት 356.6 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 836.4 ሚሊዮን ኩንታል ከፍ ብሏል። "የትኛውም መሬት ፆም አያድርም" በሚል መርህ በተከናወነ ሥራ፣ 2017 የምርት ዘመን አጠቃላይ የግብርና ምርት 1.57 ቢሊዮን ኩንታል ደርሷል። በተለይም የስንዴ ምርት በየዓመቱ 49 በመቶ ዕድገት በማሳየት፣ ሀገሪቱ የምግብ ሉዓላዊነቷን ከማረጋገጥ ባለፈ ስንዴን ለውጭ ገበያ ማቅረብ አስችሏታል ። ከዚህ በተጨማሪ የሩዝ ምርት 3 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 63 ሚሊዮን ኩንታል፣ የቡና ምርት ደግሞ ወደ 11.5 ሚሊዮን ኩንታል አድጓል።

መንግሥት በይፋ ተግባራዊ ያደረገው "የሌማት ትሩፋት" መርሃ-ግብር የእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርትን በማሳደግ ረገድ ተምሳሌታዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። በወተት፣ በዶሮ፣ በማርና በዓሳ ልማት የታየው ውጤት የኢኮኖሚ ነፃነትን ለማረጋገጥ ዓይነተኛ ድርሻ አለው። በተመሳሳይ በከተማ ግብርና ረገድ የተከናወኑ ተግባራት የከተሞችን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ የጓሮ ሜዳዎችንና የሕንፃ ጣራዎችን ለምርታማነት እንዲውሉ በማድረግ የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም እና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት መንግሥት ግብርናን ማዘመንና የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫው አድርጓል። ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ማስፋፋት፣ የግብርና ፋይናንስ አቅርቦትን ማሻሻልና የግል ዘርፉን ተሳትፎ ማሳደግ ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው። የመስኖ አቅምን በማጎልበት ግብርናን ከዝናብ ጥገኝነት የማላቀቅ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል። እንዲሁም "ከእርሻ እስከ ጉርሻ" ያለውን የዕሴት ሰንሰለት ለማዘመን ዲጂታል ቴክኖሎጂንና ሜካናይዜሽንን በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል ታቅዷል።

መንግሥት የጀመረውን የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ በማጠናቀቅ ግብዓቱን በሀገር ውስጥ ለማምረት በዝግጅት ላይ ይገኛል። ዛሬ የተመዘገቡት ውጤቶች የነገው ብሩህ ጉዞ መሠረት ናቸው። መንግሥት ኢትዮጵያን ከተረጂነት ወደ አምራችነት፣ ከምግብ ዋስትና ወደ ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማሸጋገር የገባውን ቃል በተግባር እየፈጸመ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም