ቀጥታ፡

ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ማንኛውንም ግዳጅ በብቃት መወጣትና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ተችሏል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፦ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ማንኛውንም ግዳጅ በብቃት መወጣትና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚችል የፖሊስ ኃይል መገንባቱን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡ 

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲካሄድ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉ ተጠቅሷል። 

ኮሚሽኑ በዘመናዊ አድማ ብተና የሰለጠኑ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ምረቃ ሥነ ሥርዓት ኮልፌ በሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ማሰልጠኛ ግቢ የተለያዩ የአድማ መከላከል፣ የተሽከርካሪ እና ልዩ ልዩ ወታደራዊ ትርኢቶች አቅርቧል።


 

በመርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ  የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ  ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ርዕስቱ ይርዳው፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ቃል አቀባይ ረዳት ኮሚሽነር ሞገስ ቸኮል፣ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ተወካይ ታምራት ሙልጌታ(ዶ/ር) እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ ባለፉት ዓመታት ጠንካራ ሥራዎችን በማከናወን የተሰጡትን ተልዕኮዎች በብቃት ሲወጣ ቆይቷል። 

በዚህም በሀገር ደረጃ የተሻለ ሰላምና ደኅንነት እንዲኖር ማስቻሉን ጠቁመው፤ ይህንንም ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት እውን ማድረጉን አንስተዋል።


 

ጠንካራ መንግሥትና ሕዝብ ያላት ሀገር ጠንካራ የፖሊስ ሠራዊት ሊኖራት እንደሚገባ ገልጸው፣ በዚህም ባለፉት ዓመታት የሰለጠነ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚሰጠውን ማንኛውንም ግዳጅ መወጣትና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚችል የፖሊስ ኃይል መገንባት መቻሉን ጠቁመዋል።

ዛሬ የተመረቁትም በሀገር ውስጥ የሰለጠኑ፣ የበቃ የፖሊስ ኃይል በተለይም የአድማ ብተና ኃይል፣ አድማን በዘመናዊ መንገድ መከላከል የሚያስችል አቅም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ ፖሊስ በወሰዳቸው ጠንካራ ሥልጠናዎች የበቃ የሰው ኃይል መፈጠሩንና በቁጥሩም በአቅሙም ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል። 

እንዲሁም የሎጂስቲክስ አቅማቸው ያደጉ ሀገራት የሚጠቀሙባቸው ዘመናዊ የአድማ ብተና ተሽከርካሪዎች፣ ድሮኖችና ሌሎች ትጥቆች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ይህንን ማከናወን የሚችል የሰው ኃይል ባለቤት መሆን መቻሉንም ገልጸዋል። 

በዚህም ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂና የሎጂስቲክስ አቅም እንዲሁም የታጠቃቸውን ዘመናዊ መሣሪያዎች በመጠቀም የመላው ሀገሪቱን ደኅንነት እያረጋገጠ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም