ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው ለሀገራዊ መግባባትና ለሰላማዊ ምክክር ሂደት ስኬታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው ለሀገራዊ መግባባትና ለሰላማዊ ምክክር ሂደት ስኬታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፦ ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው ለሀገራዊ መግባባትና ለሰላማዊ ምክክር ሂደት ስኬታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የሀገር ባለውለታ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት የዘገየ አስፋው ሥርዓተ ቀብር በዛሬው ዕለት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።
በሥርዓተ ቀብሩ ላይ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የጠቅላይ ሚኒስትር የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያን ጨምሮ ከፍተኛ የፌደራል እና የክልል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ለኮሚሽነር ዘገየ አስፋው በሰጡት ምስክርነት፣ ግለሰቡን በሁለት ታላላቅ የታሪክ ምዕራፎች ውስጥ የነበሩ "የጽናት ተምሳሌት" መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ፣ በወጣትነት ዘመናቸው ለአርሶ አደሩ ድምፅ በመሆን ለማኅበራዊ ፍትሕ የቆሙ የለውጥ ኮከብ እንደነበሩ አውስተዋል።
በሁለተኛውና በአሁኑ ምዕራፍ ደግሞ፣ "አገልግያለሁ ይበቃኛል" ሳይሉ የሀገሪቱን ሰላም በምክክር ለማምጣት በሰሩት ስራ የሀገር ፍቅራቸውን በተግባር ማሳየታቸውን ተናግረዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር)፣ ከኮሚሽነር ዘገየ አስፋው ጋር የቆየ ትውውቅ እንደነበራቸው ገልጸዋል።
ኮሚሽነሩ ታሪካዊውን "የመሬት ላራሹ" አዋጅ ተረቆ እንዲጸድቅና በሥራ ላይ እንዲውል በማድረጋቸው ረገድ የማይተካ ሚና የተጫወቱ የሀገር ባለውለታ መሆናቸውን መስክረዋል።
ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው በስራ መስካቸውም ሆነ በተማሪነት ዘመናቸው የነበራቸውን ጠንካራ ስብዕና የቅርብ ወዳጆቻቸው መስክረዋል።
የቀድሞው የቀዳማይ ኃይለ ሥላሴ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት የክፍል ጓደኛቸው አባቢያ አባጆቢር አባጅፋር፣ ኮሚሽነሩ በትምህርታቸው እጅግ ጎበዝ እንደነበሩና በሥራ ዘመናቸውም "የመሬት ላራሹ" አዋጅ እንዲጸድቅ በማድረግ በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት ላይ የማይረሳ አሻራ ማኖራቸውን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ አቶ አድማሱ ካሳ፤ ግለሰቡ በሥራቸው ታታሪና ውጤታማ እንደነበሩ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።