የምርምር ማዕከሉ የመድኃኒት ምርምርና ስርጸት ውጤታማነትን የሚያሳድግ አዲስ አቅም እየፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምርምር ማዕከሉ የመድኃኒት ምርምርና ስርጸት ውጤታማነትን የሚያሳድግ አዲስ አቅም እየፈጠረ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፦በአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት የተገነባው የምርምር ማዕከል የመድኃኒት ምርምርና ስርጸት ውጤታማነትን የሚያሳድግ አዲስ አቅም መፍጠሩን የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር መሳይ ወልደማርያም ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት በዘመናዊ መልክ የተገነባውን የምርምር ማዕከል መጋቢት 26 ቀን 2018 ዓ.ም መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
በአርማወር ሐንሰን የምርምር ተቋም ቅጥር ግቢ የተገነባው ዘመናዊ ተቋም ከመሠረተ ልማት ግንባታ ባለፈ፤ ራሷን የቻለችና ጤናማ የሆነች ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ የሚተጋ የላቀ የዕውቀት ማዕከል ነው።
የምርምር ማዕከሉም 40 ላቦራቶሪዎችን፣ የላቁ የጂኖሚክስ እና የባዮ ኢንፎርማቲክስ፣ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶችን ጥራትና ብቃት የሚያረጋግጥ የባዮ ኢኩዊቫለንስ ማዕከላትን አካቷል።
የተለያዩ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎችም በአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት በዘመናዊ መልክ የተገነባውን የምርምር ማዕከል ጎብኝተዋል።
የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር መሳይ ወልደማርያም፤ ጉብኝቱ የሚበለፅጉ የምርምር ውጤቶች ሽግግር ውጤታማነትን ለማስጠበቅ ያለመ ነው ብለዋል።
ማዕከሉ የመድኃኒት ምርምርና ስርጸት ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ከፍተኛ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።
በማዕከሉም የመድኃኒት ምርምርና ስርጸት ሥራዎችን በላቀ መንገድ ማከናወን የሚያስችል አዲስ አቅም መፍጠር እንደተቻለ ተናግረዋል።
በምስራቅ አፍሪካ ብቸኛው የመድኃኒት ተነጻጻሪነት ፍተሻ በማዕከሉ መገንባቱም ከኢትዮጵያ ባሻገር ለአፍሪካ ሀገራት ጭምር የላብራቶሪ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል አንስተዋል።
የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት የሀገር በቀል ዕውቀቶችን መነሻ በማድረግ የተለያዩ በሽታዎችን ሕክምና መስጠት የሚያስችሉ ስምንት የምርምር ውጤቶች መበልፀጋቸውን ገልጸዋል።
በምርምር የበለፀጉ ውጤቶችም እንደ ዋና ንጥረ ነገር የሚያገለግሉና ክትባትን በተሻሻለ ቴክኖሎጂ መስጠት የሚያስችሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አምራቾች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ታደሰ ተፈሪ፤ በኢትዮጵያ በፖሊሲ ማዕቀፍና በተለያዩ የማሻሻያ እርምጃዎች የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።
የምርምር ማዕከሉም የኢትዮጵያን የጤና ዘርፍ የጥናትና ምርምር ውጤታማነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ የባህል ሕክምና አዋቂዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት መጋቤ ጥበብ መሪጌታ መንግስቱ ደስታ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ የባህል ሕክምና ውጤታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ማዕከሉ በዘርፉ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎችን የሚያግዝ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ አነስተኛ መድኃኒት አምራቾች ዘርፍ ማኅበር ፕሬዝዳንት ሀሺም አሕመድ ናቸው።
የዜኒት ገብስ እሸት ኢትዮጵያ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰለሞን ገብረእግዚእ በበኩላቸው፤ በማዕከሉ የተፈጠረው የምርምር ምኅዳር የመድኃኒት አምራቾችን አቅም ለማጎልበት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።