የምርጫ ሂደቱ ምቹ የፉክክር ድባብ የተፈጠረበት ነው- የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
የምርጫ ሂደቱ ምቹ የፉክክር ድባብ የተፈጠረበት ነው- የፖለቲካ ፓርቲዎች
ባህር ዳር፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፦ የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ከመሆኑም ባሻገር ምቹ የፉክክር ድባብ የተፈጠረበት መሆኑን በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሂደቱም ሆነ በውጤቱ የህዝብን አመኔታ ያተረፈ እንዲሆን፣ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አቋቁመው በትብብር እየሰሩ ይገኛሉ።
እስካሁን ባለው የእጩዎችና የመራጮች ምዝገባ፣ ብሎም የምረጡኝ ቅስቀሳው ጥሩ ሂደት ላይ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ምክትል ሊቀመንበር መልካሙ ፀጋዬ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ለዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅትም ፓርቲው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓም ለሚካሔደው ጠቅላላ ምርጫ በቂ ቁጥር ያላቸው እጩዎችን ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።
ፓርቲው ለሀገርና ለህዝብ የሚበጁ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችንና ፕሮግራሞችን የማስተዋወቅ ስራ በስፋት እየሰራ እንደሚገኝም ነው ያነሱት።
በቅስቀሳው ወቅትም ከስሜት ቀስቃሽ ሃሳቦችና አስተያየቶች በመቆጠብ፣ የምርጫ ህጉን ብቻ መሰረት በማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በምርጫው አሸናፊ ሆኖ ለመገኘትም፣ የተመቻቸውን የመገናኛ ብዙሃን የሰዓት ድልድል በመጠቀም የምረጡኝ ቅስቀሳና ክርክር እያካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላማዊና አሳታፊ በሆነ መንገድ እንዲከናወን እየሰራን ነው ያሉት ደግሞ የአማራ ዴሞክራሲ ሃይሎች ንቅናቄ (አዲሃን) ስራ አስፈፃሚ አባል አዲሱ ጉልላት ናቸው።
ለምርጫው በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ፣ በፀጥታና መሰል ዘርፎች አማራጭ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ለህዝብ ለማስተዋወቅ በመገናኛ ብዙሃን ሰፊ እድል መፈጠሩንም ተናግረዋል።
እስካሁን ባለው እንቅስቃሴ ምንም ዓይነት የማዋከብና የማንገላታት ችግር እንዳልደረሰባቸው አመልክተው፤ ይህም ምርጫውን ዴሞክራሲያዊ በሆነ አግባብ ለማጠናቀቅ አስቻይ ሁኔታ መኖሩን የሚያመላክት ነው ብለዋል።
ምርጫ ለአንድ ሀገር ህጋዊና በህዝብ ይሁንታን ያገኘ መንግስት ለማቋቋም ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ እንዲሳካም ፓርቲያቸው ሰላማዊ የትግል አማራጭን በመከተል እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሰሜን ኢትዮጵያ አስተባባሪ ኃይለማርያም ብርሃኑ በበኩላቸው፤ ለምርጫው ስኬታማነት በጋራ ምክር ቤት ውስጥ ታቅፈን በትብብር እየሰራን ነው ብለዋል።
በመሆኑም ከምርጫ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የሚገጥሙ ችግሮች በሰለጠነ አግባብ እየተፈቱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም እስከ መጨረሻው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።