ቀጥታ፡

የዱር እንስሳትን እና መኖሪያ አካባቢያቸውን የመጠበቅና የማልማት ሥራ ይጠናከራል

ሮቤ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፦ የዱር እንስሳትና መኖሪያ አካባቢያቸውን በመጠበቅና በማልማት ለቱሪዝም መስህብነት የማዋል ሥራው እንደሚጠናከር የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ገለጸ።

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጥበቃን ይበልጥ ለማጠናከር ታሳቢ ያደረገ ሁለተኛው ዙር የዱር ሕይወት ጠባቂዎች (ሬንጀሮች) ምረቃ ተካሂዷል።  


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ እንደገለጹት፤ የዱር እንስሳትና መኖሪያ አካባቢያቸውን በመጠበቅና በማልማት ለቱሪዝም መስህብና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የማዋል ሥራ በትኩረት እየተከናወነ ነው።

ባለስልጣኑ የሀገሪቱን የተፈጥሮ ጸጋዎች ለላቀ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማዋል፣ የዱር እንስሳትንና መኖሪያ አካባቢያቸውን የመጠበቅና የማልማት ሥራን በልዩ ትኩረት እያከናወነ መሆኑን አስታውሰው፣ ይህም የቱሪዝም መስህብነትን በማሳደግ ረገድ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

ባለሥልጣኑ ባለፉት ስልሳ ዓመታት የዱር እንስሳትና መኖሪያ አካባቢያቸው ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፉ የተለያዩ የጥበቃና የልማት ሥራዎችን ሲያከናውን እንደቆየና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል።

በፓርኮች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ተፅዕኖዎችን በመከላከል የጥበቃና የልማት ሥራዎችን ይበልጥ ለማጠናከር በተከናወኑ ሥራዎች አበረታች ለውጦች እየተመዘገቡ መምጣታቸውንም አመልክተዋል። 


 

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ለማልማትና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ይበልጥ ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ የኢኮ-ቱሪዝምና ሌሎች የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች የጥረቱ ማሳያዎች እንደሆኑም አንስተዋል። 

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፣ የዱር ሕይወት ጠባቂዎች (ሬንጀሮች) መመረቅ በዘርፉ የሚታዩ ህገወጥ ተግባሮችን ለመከላከልና የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ሥራውን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል ነው።

የዱር እንስሳትና የመኖሪያ አካባቢያቸውን ከጥፋት ለመታደግ ከዘላቂ የቱሪዝም ልማት ጋር በማጣመር ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲውሉ ማድረግ ይገባል ሲሉም ዳይሬክተሩ አመልክተዋል። 

የባሌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም ኃይሌ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ብሔራዊ ፓርኩን ከተለያዩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ለመከላከል ከፓርኩ አስተዳዳርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው። 


 

በዚህም ከዚህ በፊት ይስተዋሉ የነበሩ ተግዳሮቶች እየቀነሱ፤ የጥበቃና የልማት ተግባራትም እየተሻሻሉ መጥተዋል ብለዋል።

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ ሻሚል ከድር በበኩላቸው፤ በፓርኩ ለሦስት ወራት በጥበቃና ሌሎች መሰል ሥራዎች ላይ ስልጠና የወሰዱ 44 ሬንጀሮች መመረቃቸውን ገልጸዋል።  


 

ሬንጀሮቹ በጥበቃ ሳይንስ፣ በስና ምግባር፣ በአካል ብቃትና ሌሎች ክህሎቶችን ማግኘታቸውን ተናግረዋል። 

ተመራቂ ሬንጀሮች በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፤ የወሰዱት በተግባር የተደገፈ ዘመናዊ ሥልጠና በእውቀት ላይ የተመሰረተ የጥበቃ ሥራን ለማከናወን እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል። 

ለሥልጠናው መሳካት አስተዋጽኦ ለነበራቸው አካላት እውቅናና የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን የተለያዩ ባለድርሻ አካላትም ፓርኩን ጎብኝተዋል።

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የዓለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የደጋ አጋዘን፣ ቀይ ቀበሮና ሌሎች በርካታ የዱር እንስሳትና ዕጽዋት መገኛ ነው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም