ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ዕውን ሆነዋል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ዕውን መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በልደታ ክፍለ ከተማ የተገነባውን 29ኛው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡


 

በምርቃት ሥነ-ስርዓቱ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት፤ መዲናዋን ውብ ገፅታ ከሚያላብሱ የልማት ውጤቶች ባሻገር ውጤታማ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

በልደታ ክፍለ ከተማ ለአገልግሎት የበቃውን 29ኛ የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ጨምሮ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች ዕውን መሆናቸውን ገልጸዋል።

በልደታ ክፍለ ከተማ በጎነት መንደር ላይ የተገነባው የምገባ ማዕከልም የአገልግሎት አቅምና ተደራሽነት በማስፋት ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው የሀገር ባለውለታዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።


 

ዳሸን ባንክ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት በጎነት ሰፈር 29ኛውን የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል በማስገንባት ላሳየው ቁርጠኝነት ምስጋና አቅርበዋል።

በቅርቡ  ሁለት የምገባ ማዕከላት ወደ ሥራ እንደሚገቡም  አረጋግጠዋል።

የልደታ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ልዕልቲ ግደይ በበኩላቸው፤ የምገባ ማዕከሉ ለክፍለ ከተማው 3ኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ የምገባ ማዕከል ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በቀን አንድ ጊዜ ማዕድ እንደሚቋደሱ ገልጸዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የማዕከሉ ተጠቃሚ ወይንሸት ከበደ እንዳሉትም፤ የምገባ ማዕከሉ የአቅመ ደካሞችን የኑሮ ሸክም የሚያቃልል ነው።


 

ሌላኛው የማዕከሉ ተጠቃሚ ዘካሪያስ ገዝሙ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ መንግስት የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።

በበጎነት መንደር የተገነባው 29ኛ የምገባ ማዕከልም የበርካታ እጅ አጠር ዜጎችን የኑሮ ጫና የሚቀንስ ነው ያሉት ደግሞ አካሉ ከፈለኝ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም