ቀጥታ፡

የከተማ ግብርናን ከጤና ሙያው ጋር ያጣመረው ወጣት

በቀደሰ ተክሌ (ከሚዛን አማን)

የሰው ልጅ የሕይወት ኡደት በጊዜ የታጠረ ነው። የሰውነት ሚዛን ተለክቶ ውብ ሆኖ የሚገኘው ደግሞ በዚህ የጊዜ ምጣኔ ውስጥ ስኬታማ ሥራ ሰርቶ ተገቢው ቦታ ላይ ሲገኙ ብቻ ነው።

ጠንካራ ሰዎች በዕድሜ ዘመናቸው የተሰጣቸውን ጊዜ በአግባቡ ተጠቅመው ስኬት ላይ ይደርሳሉ። ለጊዜ ብዙም ትርጉምና ዋጋ የማይሰጡ ሰዎች ደግሞ እንቅስቃሴያቸውን በጊዜ ስለማይገደብና በዚያው ልክ ተሯሩጠው ስለማይሰሩ ስኬታማ ሳይሆኑ ዘመናቸውን በችግር ያሳልፋሉ። ሰው ሲፈጠር ይህን በማመዛዘን የተሻለውን መንገድ ይጠቀም ዘንድ ደግሞ አዕምሮ ተሰጥቶታል።

ማንም ሰው በኑሮ ከመመራት ይልቅ ራሱ ኑሮን መምራት የሚችለው ጠንክሮ ሲሰራ ነው። የአንድ ጠንካራ የሥራ ሰው አንዱ መለኪያ ደግሞ የጊዜ አጠቃቀሙ ነው። ጊዜውን በማብቃቃት ካለው ሥራ ተጨማሪ ሥራ ፈጥሮ የሚሰራና ለበለጠ የሚተጋ ስኬታማ ሕይወትን መምራት ይችላል።

በሚዛን አማን ከተማ ኢዜአ ያነጋገርው ወጣት ይህን በተግባር በማረጋገጥ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነው። ወጣት ዳዊት ባይቴንስ ይባላል። ከተሰማራበት የጤና ዘርፍ ጎን ለጎን ባለው ትርፍ ጊዜ በከተማ ግብርና ሥራ ተሰማርቶ ተጠቃሚነቱን እያሳደገ ይገኛል።  

ሰርቶ ለመለወጥ ካላው ፍላጎትና ቁርጠኝነት የተነሳ በሕይወቱ ምንም አይነት ጊዜ እንዲባክንበት አይፈልግም። እያንዳንዷን ሰዓትና ደቂቃ ትርጉም ባለው መልኩ ለሥራ ያውላል። ይህ የመነጨው ደግሞ ከሥራ ወዳድነቱ ነው። ሲሰራ ውሎ ሲሰራ ቢያድር ደከመኝና ሰለቸኝን አያውቅም።

ለእዚህ ባህሪው እርሾ የሆነው ደግሞ በልጅነቱ ወላጆቹን በግብርና ሥራ እያገዘ ማደጉ ነው። በትምህርቱም ወደ ኋላ ሳይል ጠንክሮ በመማር ስኬታማነቱን አስመስክሯል። 

የኮሌጅ ትምህርቱን በፋርማሲ የተመረቀው ወጣቱ በአሁን ወቅት በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ቲቺንግ ሆስፒታል በጤና ባለሙያነት እየሠራ ይገኛል። የጤና ተቋም ሥራው ቀንና ማታ በፈረቃ የሚሰራ በመሆኑ ከሆስፒታል ሥራው ውጪ ሲሆን ከተማ ወጥቶ በመዝናናት አሊያም በዋዛ ፈዛዛ የሚያሳልፈው ጊዜ የለውም።

ከጤና ሥራው ጎን ለጎን በቤቱ ዙሪያ ያለውን ባዶ መሬት እያለማ ይገኛል። የከተማ ግብርናና የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቮችን ተከትሎ በተለይ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ይህን የግብርና ልማት ስራውን አጠናክሮ ቀጥሏል።

የግብርና ሥራውን የጀመረው በጤና ሙያ ሥራው በወር ከሚያገኘው ደመወዝ ባሻገር ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለማግኘት አስቦ ነው። "የግብርና ምርቱ ለቤት ውስጥ ፍጆታ ባውለው እንኳ ወጪዬን ይቀንሳል" የሚለውም ሌላው መነሻ ምክንያቱ ነበረ።

በዚህም ባለው ጠባብ መሬት ላይ ቆስጣ፣ ጥቅል ጎመን፣ ካሮትና መሰል የጓሮ አትክልቶችን አልምቶ በመጠቀም "ምግቤን ከጓሮዬ" የሚለውንም ንቅናቄ በተግባር አሳይቷል። በጓሮ ያለማቸውን ምርቶች ለቤተሰብ ፍጆታ ማዋሉም ከወጪ እንደታደገው ነው የገለጸው።

የአካባቢው መሬት ያለስስት ከሚያበቅላቸው ፍራፍሬዎች መካከል ሙዝ በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ወጣት ዳዊትም በጓሮ አትክልት የጀመረውን ሥራ በማስፋት በቤቱ ዙሪያ የሙዝ ልማት ስራውን አጠናክሯል። የሙዝ ምርቱም ከቤት ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለገበያም እያቀረበ ነው። ዛፉም ጥላ ሆኖ እያገለገለው ነው።

ሁሌም ለተጨማሪ ሥራ የሚተጋው ይህ ባለ ራዕይው ወጣት ምርጥ የቡና ዘር ከግብርና ባለሙያዎች በመውሰድ ችግኝ አዘጋጅቶ ለአርሶ አደሮች ያሰራጫል። አምና የቡና ችግኝ ተከላ ወቅት ከ15 ሺህ በላይ የቡና ችግኞችን በጓሮው አዘጋጅቶ በመሸጥ ተጠቃሚ ሆኗል። ከጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ባሻገር በቆሎ በማልማትም ተጠቃሚነቱን እያሳደገ ነው።

ወጣት ዳዊት ባለው ጠባብ የከተማ ማሳ ላይ እነዚህን ልማቶች እያከናወነ ያለው በአንድ ጊዜ አይደለም። እንደ የአዝመራው ተስማሚነት አፈራርቆ የማልማት ጥበብንም ተክኗል። በቆሎ ደርሶ የተነሳበት ማሳ ላይ ሌሎች አትክልቶችን ያለማል። በሌላ በኩል ደግሞ ጥምር የእርሻ ሥርዓትን በመከተል በሙዝና ሌሎች ፍራፍሬዎች ስር ባለ ክፍት ቦታ ላይ ቡና ያለማል፤ የአትክልት ችግኞችንም ያዘጋጃል። 

ይህ ብልህነት የተሞላው የከተማ ግብርና ልማት ሥራው የከተማ ቤቱን የገጠር ሞዴል አርሶ አደር ማሳ አስመስሎታል።

ወደፊት የተቀናጀ የግብርና ልማት ጣቢያን የመፍጠር ዓላማ እንዳለው የገለጸው ወጣቱ፣ በቅርቡም በንብ ማነብ ሥራ ውስጥ ለመሰማራት እየተዘጋጀ መሆኑን ነው የተናገረው። ለዚህም የቀፎ ግዥና የቀፎ ማስቀመጫ ቦታ ዝግጅት ሥራ ላይ ይገኛል። 

በአሁኑ ወቅት በገበያ እየታየ ያለውን የዋጋ ንረት መቋቋም የሚቻለው ሰርቶ ውጤታማ ሲኮንና ገቢን ማሳደግ ሲቻል ነው የሚል እምነት አለው። ወጣቱ እንደሚለው ምርት የሚያመርት ሰው እየበዛ ሲመጣ ገበያው ይረጋጋል። በመሆኑም ሰዎች ሁሉንም ነገር ከገበያ ከመግዛት ይልቅ ባላቸው ትንሽ መሬት ላይ የተወሰነ ምርት በማምረት ለቤት ውስጥ ፍጆታ እንዲጠቀሙ ይመክራል።

ከመደበኛ የመንግሥት ሥራው ጎን ለጎን የተሰማራበት የከተማ ግብርና ልማት ሥራ ወጪውን ከመቆጠብ አልፎ ተጨማሪ ገቢ እያስገኘለት በመሆኑ በቀጣይም ልማቱን ለማጠናከር ሞራል እንደሆነው ተናግሯል።

እሱ እንደሚለው ከሆነ በአካባቢው በርካታ ወጣቶች የቤተሰቦቻቸውን ማሳ ትተው በከተማ ያለ ሥራ ጊዜያቸውን ሲያሳልፉ ማየት የተለመደ  ነው። ነገር ግን ነገን የተሻለ ለማድረግ ዛሬ የወጣትነት ጊዜን ጠንክረን ልንሰራ ይገባል ይላል። ወጣቶችም ያላቸውን ጉልበትና ጊዜ በመጠቀም ሀብት ማፍራት የሚያስችላቸውን ሥራ መሥራት እንዳለባቸው ይመክራል። በተለይ የእርሻ መሬት ያላቸው ወጣቶች በግብርና ሥራ ራሳቸውን መለወጥ፣ ቤተሰቦቻቸውን መመገብ፣ ገበያ ማረጋጋትና በሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ውስጥ አሻራቸውን ማሳረፍ እንዳለባቸው ነው የገለጸው።

የሚዛን አማን ከተማ ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ኅብረት ሥራ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘሪሁን መንግሥቱ የወጣት ዳዊት ታታሪነት ለብዙዎች ተሞክሮ እንደሚሆን ነው የገለጹት።

በተለይ የከተማ ግብርናና የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቮችን መሠረት በማድረግ ያከናወናቸው ተግባራት በትንሽ መሬት መስራት ከተቻለ ገበያን ማረጋጋት እንደሚቻል በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል። ጽህፈት ቤቱ ወጣቱንና የእሱን ፈለግ ተከትለው የሚሠሩ ወጣቶችን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ኃላፊው እንዳሉት በአሁኑ ወቅትም በሌማት ትሩፋት የሥራ ዘርፎች ወጣቶች በብዛት እንዲሰማሩ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው። በራስ ተነሳሽነት ያላቸውን ጊዜ አብቃቅተው ወደልማት የገቡ እንደ ወጣት ዳዊት ያሉ ወጣቶች ቢበራከቱ ለግብርናው ዘርፍ ኢኮኖሚ የሚኖራቸው አዎንታዊ ሚናም የጎላ ነው።

ማንም ሰው ኑሮን አሸንፎ ወጤታማ ለመሆን እንደ ወጣት ዳዊት በሥራ መትጋት ይኖርበታል። ወቅቱ ያለን ጊዜ አብቃቅቶ  ተጨማሪ ሥራዎች መስራት የግድ የሚልበት ወቅት ነው። ለብዙዎች በቅጥር ሰርቶ በሚገኝ ገቢ ብቻ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት አስቸጋሪ በመሆኑ አማራጮችን መጠቀም ያስፈልጋል። ለእዚህም እንደወጣት ዳዊት በዙሪያችን ምን ሀብት አለ በሚል ለይቶ ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል። ጊዜን ከጉልበት ጋር አጣምሮ መጠቀምም እንዲሁ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። 

የሰው ልጅ በሕጻንነትና በእርጅናው ዕድሜ የፈለገውን ማድረግ፣ ወጥቶና ወርዶ ሀብት ማፍራት አይችልም። ይህ የሚሆነው በወጣትነትና በጎልማሳነት ዕድሜ ብቻ ነው። በመሆኑም ለነገ ያለምነውን በጊዜው ማሳካት የምንችለው ዛሬ ጠንክረን ስንሰራ ነው። ስለዚህ የወጣትነት ዕድሜያችንን በውጤት ለማጀብ ጠንክረን ልንሠራበት ይገባል። ሥራ ክቡር ከመሆን በላይ ጠንክሮ የሰራውንም ያስከብራል፤ ይለውጣል፤ ሰላም !

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም