ቀጥታ፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ 29ኛውን የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል መርቀው ከፈቱ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ 29ኛውን የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አደረጉ።

በምርቃት ሥነ-ስርዓቱ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት፤ መዲናዋን ውብ ገፅታ ከሚያላብሱ የልማት ውጤቶች ባሻገር ውጤታማ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።


 

በልደታ ክፍለ ከተማ ለአገልግሎት የበቃውን 29ኛ የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ጨምሮ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች ዕውን መሆናቸውን ገልጸዋል።

በልደታ ክፍለ ከተማ በተገነባው የምገባ ማዕከልም የአገልግሎት አቅምና ተደራሽነት በማስፋት ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው የሀገር ባለውለታዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

ዳሸን ባንክ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት በበጎነት ሰፈር 29ኛውን የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል በማስገንባት ላሳየው ቁርጠኝነት ምስጋና አቅርበዋል።


 

በቅርቡ ሁለት የምገባ ማዕከላት ወደ ሥራ እንደሚገቡም አረጋግጠዋል።

የልደታ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ልዕልቲ ግደይ በበኩላቸው፤ የምገባ ማዕከሉ ለክፍለ ከተማው 3ኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ማዕከልም ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በቀን አንድ ጊዜ ማዕድ እንደሚቀርብ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም