በክልሉ መንግስት የገባውን ቃል በመተግበር የህዝቡን የልማት ጥያቄ ደረጃ በደረጃ እየመለሰ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ መንግስት የገባውን ቃል በመተግበር የህዝቡን የልማት ጥያቄ ደረጃ በደረጃ እየመለሰ ነው
ጂንካ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፦ የክልሉ መንግስት የገባውን ቃል በመተግበር የህዝቡን የልማት ጥያቄ ደረጃ በደረጃ እየመለሰ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ ገለጹ።
በክልሉ የአሪ ዞን ሰሜን አሪ ወረዳ ከ 57 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የተገነቡ የንፁህ መጠጥ ውሃና የሳላ ወንዝ ድልድይ ግንባታ ፕሮጀክቶች ዛሬ ተመርቀዋል።
በፕሮጀክቶቹ ምረቃ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲን ጨምሮ የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
በወቅቱም ዋና አፈ-ጉባኤ አለማየሁ ባውዲ እንደገለፁት መንግስት የገባውን ቃል በመተግበር የህዝቡን የልማት ጥያቄ ደረጃ በደረጃ እየመለሰ ነው።
ዛሬ ለአገልግሎት የበቁት የሳላ ወንዝ ድልድይ እና የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በህዝቡ ዘንድ ለረጅም ዓመታት ጥያቄ ሲነሳባቸው የነበሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
መንግስት የህዝቡን ጥያቄ በመገንዘብ አፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት ርብርብ ሲያደርግ እንደነበር ገልፀው፥ ለዚህም ዛሬ የተመረቁ ፕሮጀክቶች ማሳያ እንደሆኑም አመልክተዋል።
የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ በበኩላቸው አካባቢው ስንዴ፣ የቅባት እህሎች፣ ቅመማ ቅመምና ፍራፍሬዎች በስፋት የሚመረቱበት በመሆኑ የመንገድ ግንባታው ለማህበረሰቡ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።
በተጨማሪም በአካባቢው ቀደም ሲል ከህብረተሰቡ ጥያቄዎች ሲነሳባቸው የነበሩ የጎዛ ጊቻ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፣ የጎዞ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና ጎዛ ጤና ጣቢያ ግንባታዎች ተመርቀው ወደ አገልግሎት ገብተዋል ብለዋል።
በቀጣይም የመብራት እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚያገኙ አረጋግጠዋል።
በሰሜን አሪ ወረዳ የጎዛ ከተማ ነዋሪዎችም፤ በከተማው መብራት፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ የመንገድ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ጤና ጣቢያ እንዲገነቡ ሲጠይቁ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ከጥያቄዎቹ መካከል ንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ የሳላ ወንዝ ድልድይ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና የጤና ጣቢያ ግንባታዎች ተጠናቀው ለአገልግሎት በመብቃታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።