ቀጥታ፡

የኮሚሽነር ዘገየ አስፋው ሥርዓተ ቀብር በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት የዘገየ አስፋው ሥርዓተ ቀብር በዛሬው ዕለት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።

በሥርዓተ ቀብሩ ላይ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የጠቅላይ ሚኒስትር የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያን ጨምሮ ከፍተኛ የፌደራል እና የክልል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተገኝተዋል።

ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው በተለያዩ የመንግሥት የኃላፊነት እርከኖች እና በሰብዓዊ አገልግሎት ዘርፍ ሀገራቸውን በታማኝነት ሲያገለግሉ የቆዩ መሆናቸውን የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል። 

ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው በተለይም በኢትዮጵያ ታሪክ ቀዳሚ ስፍራ የሚሰጠው የ"መሬት ላራሹ" አዋጅ ተግባራዊ እንዲሆንና የአርሶ አደሩ የመሬት ይዞታ መብት እንዲከበር ግንባር ቀደም ሚና ከተጫወቱ ቁልፍ ሰዎች መካከል አንዱ ነበሩ።

በተለያዩ ጊዜያት በሚኒስትርነት ሀገራቸውን ያገለገሉ ሲሆን፣ በመጨረሻው የዕድሜ ዘመናቸው ደግሞ በኢትዮጵያ ለዘመናት ስር የሰደዱ መሠረታዊ ችግሮችን በሰለጠነ ውይይት ለመፍታት በተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ውስጥ በኮሚሽነርነት በማገልገል ላይ ነበሩ። 

ከፖለቲካዊ ተሳትፏቸው ባሻገር በበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ ዕድሜያቸውን ሙሉ በቁርጠኝነት ያገለገሉ መሆናቸውንም የሕይወት ታሪካቸው ያመላክታል።

ሥርዓተ ቀብራቸውም በዛሬው ዕለት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም