ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የቆዩ የሀሳብ ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ በመፍታት ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ታሪካዊ ዕድል ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የቆዩ የሀሳብ ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ በመፍታት ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ታሪካዊ ዕድል ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የቆዩ የሀሳብ ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታትና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ታሪካዊ ዕድል መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ገለጸ።
በኢትዮጵያ ለዘመናት ስር የሰደዱ የሃሳብ ልዩነቶችን በንግግር ለመፍታትና በሃሳብ የበላይነት የሚያምን ትውልድ ለመፍጠር ታቅዶ የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር፣ አሁን ላይ አዲስና ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።
ኮሚሽኑ በሁሉም ክልሎች፣ በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች፣ በፌዴራል ተቋማት እና በውጭ በሚኖሩ ዜጎች ዘንድ ያለውን የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት በስኬት አጠናቋል።
ከወረዳ ጀምሮ እስከ ማዕከል ድረስ በግልጽነት በተከናወነው በዚህ ሂደት፣ ለዋናው ሀገራዊ ጉባኤ የሚሳተፉ ተወካዮች ተለይተዋል።
ለምክክሩ ከተለያዩ ማህበረሰቦች አሳታፊ በሆነ መልኩ ግብዓቶች የተሰበሰበ ሲሆን፤ ይህ ተግባር ኮሚሽኑ ወደ ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ መሸጋገር የሚያስችለውን አስተማማኝ መሠረት ጥሏል።
በአሁኑ ወቅት ኮሚሽኑ ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለማካሄድ የሚያስችሉ የዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
ይህም ኢትዮጵያ ልዩነቶቿን በሰለጠነ መንገድ በመፍታት የተሻለች ሀገር ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት የሚያሳይ ነው።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አሕመድ ሁሴን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ ሀገራዊ ምክክሩ ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባትና ለቀጣዩ ትውልድ የምትመች ሀገር ለማስረከብ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡
በውይይት የምትጸና ሀገር ሁለንተናዊ ጥንካሬ ከመጎናጸፏ ባለፈ ዜጎቿን ለላቀ ተጠቃሚነትና ለጋራ ብልፅግና የምታበቃበት ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል፡፡
ይህ የታሪክ ምዕራፍ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ ብሎም ለሀገር ግንባታ አስተማማኝ መሠረት የሚጥል መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘላቂ ሀገራዊ መግባባትን ለማጎልበት በሚከናወኑ ስራዎች የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለምክክሩ ስኬትም ያልተቋረጠ ተሳትፎ እና ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሰላማዊ የውይይት ባህል እንዲዳብርና ሀገራዊ መግባባት እንዲሰፍን እያከናወኑት ያለው የላቀ ሚና በቀጣይም በታላቅ ተነሳሽነት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የበለጸገች ሀገርን በጋራ ለመገንባት ያለውን መልካም ዕድል በመጠቀም እያንዳንዱ ዜጋ ያለውን ሚና በተሻለ መንገድ እንዲያበረክትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መላው ህዝብ በታላቅ የኃላፊነት ስሜትና በንቁ ተሳትፎ በሂደቱ ሲሳተፍ እንደነበር ጠቅሰው አሁንም ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የደረሰው የምክክር ሂደት በስኬት እንዲጠናቀቅ አበርክቶውን ማጣናከር ይገባዋል ነው ያሉት፡፡