ቀጥታ፡

በባህር ዳር ከተማ ባለፉት 10 ወራት ከ47 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል

ባህርዳር ፤ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፡-በባህርዳር ከተማ ባለፉት 10 ወራት ከ47 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን የከተማ አስተዳደሩ ስራና ክህሎት መምሪያ ገለጸ።

የመምሪያው የሥራ ዕድል ፈጠራ ቡድን መሪ አቶ ጥላሁን ሊበን እንደገለጹት፤ የስራ እድል ፈጠራው በከተማዋ በሚካሄዱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልማት ስራዎችን ጨምሮ ያሉ ጸጋዎችን በመጠቀም የተካሔደ ነው።

በበጀት ዓመቱ  ከ45 ሽህ 300 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር የታቀደ ሲሆን ባለፉት አስር ወራት  ብቻ ከእቅድ በላይ ከ47 ሽህ 300 ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥም  ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ቋሚ የስራ እድል የተፈጠረላቸው ዜጎች መሆናቸውን አመልክተው 18 ሺህ 300 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ሴቶች ናቸው ብለዋል።

የስራ እድሉን መፍጠር የተቻለውም በኮንስትራክሽን፣ በአገልግሎት፣ በኢንዱስትሪ፣ ግብርናና ሌሎች የልማት ዘርፎች መሆኑን አስረድተዋል።

በከተማዋ የተፈጠረው ሰላም የልማት ስራዎች በስፋት እንዲከናወኑ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩ በዘርፉ ከእቅድ በላይ አፈፃፀም ለማስመዝገብ እንዳስቻለም  ነው ያመለከቱት።

የስራ እድሉ የተፈጠረላቸው ዜጎች ፈጥነው ወደ ስራ እንዲገቡ ከአበዳሪ ተቋማት ጋር በትብብር የተሰራ ሲሆን ከ62 ሚሊዮን ብር በላይ በመደበኛና ተዘዋዋሪ ብድር እንዲያገኙ መደረጉንም አንስተዋል።


 

ሀያት፣ ሶፊያና ጓደኞቻቸው የዶሮ ርባታ ሽርክና ማህበር ስራ አስኪያጅ ወጣት ኢብራሄም አደም እንደገለጸው፣ በሶስት አባላት የጀመሩት ስራ አሁን ላይ ለሌሎች የስራ እድል ለመፍጠር ችሏል።

መንግስት ለስራ እድል ፈጠራ የሰጠው ትኩረት የሚደነቅ እንደሆነ ገልጾ እየተደረገ ያለው ሙያዊ ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ መቀጠል አንዳለበት አመላክቷል።

"ገበየሁና ታደለ" የልብስ ስፌት ሽርክና ማህበር ስራ አስኪያጅ ወጣት ገበየሁ አንበሳው እንዳለው፣ በመንግስት የተመቻቸላቸውን 450 ሺህ ብር ብድር በመጠቀም ውጤታማ ለመሆን እየሰሩ ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም