በመስዋዕትነት የዘለቀው የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ምሉዕ የሚሆነው የብልፅግና ተምሳሌትነቷ ሲረጋገጥ ነው-ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በመስዋዕትነት የዘለቀው የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ምሉዕ የሚሆነው የብልፅግና ተምሳሌትነቷ ሲረጋገጥ ነው-ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፡-በመስዕዋትነት የዘለቀው የኢትዮጵያ ነፃነትና ሉዓላዊነት ምሉዕ የሚሆነው የብልፅግና ተምሳሌትነቷ ሲረጋገጥ ነው ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና በግብርና ሚኒስቴር ትብብር "ከተረጅነት ወደ ምርታማነት" በሚል መሪ ሃሳብ በሐዋሳ ከተማ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይና የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ተገኝተዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ሱሩርና ሌሎችም የሥራ ኃላፊዎችና የግብርና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ የመወያያ ፅሁፍ ያቀረቡት ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) የተሟላ ሉዓላዊነት ሀገራዊ ክብር የማረጋገጥ ጉዞ አካል ነው ብለዋል።
በመሆኑም በመስዕዋትነት የዘለቀው የኢትዮጵያ ነፃነትና ሉዓላዊነት ምሉዕ የሚሆነው የብልፅግና ተምሳሌትነቷ ሲረጋገጥ እንደሆነም ገልፀዋል።
ከተረጂነት መላቀቅ የብሔራዊ ጥቅም አካል ሆኖ የመንግስት ስትራቴጂክ አጀንዳ ተደርጎ በፖሊሲ አቅጣጫ እየተመራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት፣የብሔራዊ ጥቅም ሉዓላዊነት፣ የፖለቲካ ሉዓላዊነት፣ የባህልና የማንነት ሉዓላዊነት በጋራ ተሰናስለው የሀገር ህልውናን የሚያፀኑ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።
የመንግስት ኢኒሼቲቭ መነሻ ሁኔታዎችም የርሀብና ድርቅ ታሪክ ገመና ማስቀረት፣ ተረጅነት ነክ ባርነትን ማስቀረት፣ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን በራስ አቅም ለመመከት ያለውን ሚና አንስተዋል።
ከነዚህ መካከል የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ፣ ከውጭ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት፣የውጭ ምንዛሬና የወጪ ንግድ ሚዛን መጠበቅ እንዲሁም በቤተሰብ ደረጃ ብልፅግናን ማረጋገጥ በሚሉ ግቦች ላይ የቆመ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የተሟላ ሉዓላዊነትን ከውስጥ ወደ ውጭ የሚመለከት የፖሊሲ አቅጣጫ በመከተል የተረጅነትና የልመና አስተሳሰብን ማስወገድ፣ ህዝቡን ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር፣ የቤተሰብና የማህበረሰብ ብልፅግና ማረጋገጥና ሀገርን ከተረጅነትና ጥገኝነት ማላቀቅ የመንግስት የፖሊሲ አቅጣጫ ግቦች መካከል ለአብነት ጠቅሰዋል።
ኢኒሼቲቩ ተፈናቃዮችን፣ ዕርዳታ ተጠቃሚዎች፣የገጠርና ከተማ ሴፍትኔት ተጠቃሚዎች፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችና የስደት ተመላሾችን ጨምሮ የችግሩ ሰለባ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ነው ያነሱት።
ዜጎችን ከተረጅነት የማላቀቅ ፎኖተ ካርታ ዕውን ለማድረግ ደግሞ በየደረጃው ባለው የመንግስት መዋቅር የጋራ አረዳድና ግንዛቤ ይዞ በትጋት መስራት እንደሚገባ አንስተዋል።
እስከ አሁን እንደ ሀገር የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት አበረታች ስራዎች መከናወናቸውንና ተጨባጭ ሁሉን አቀፍ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።