ቀጥታ፡

ዜጎችን ከተረጂነት ማላቀቅ የሚያስችሉ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ዜጎችን ከተረጂነት የማላቀቅ አጀንዳን ማሳካት የሚያስችሉ ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ ገለጹ።

በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና በግብርና ሚኒስቴር ትብብር "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት" በሚል መሪ ሃሳብ በሐዋሳ ከተማ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።


 

በመድረኩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ እና የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ተገኝተዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ሱሩር እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎችና የግብርና ሙያተኞች ተገኝተዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ፣ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ ከተረጂነት የመላቀቅ አጀንዳን ማሳካት የሚያስችሉ ተጨባጭ ውጤቶች እያስመዘገበች መሆኑን ገልፀዋል።

የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ከተረጂነት ወደ አምራችነት እያሸጋገረ መሆኑን የስንዴ ምርታማነትን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ዕርዳታ የችግር ጊዜ እንጂ የኑሮ መሰረት መሆን እንደሌለበትም ጨምረው ገልፀዋል።

ዜጎችን ከተረጂነት በዘላቂነት ማውጣትና ራስን ማስቻል የህልውና ጉዳይ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ይህን ሀገራዊ ግብ በተሟላ ደረጃ ገቢራዊ ለማድረግ የሚዲያና የዘርፉ ተቋማት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።


 

የኢዜአ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደ ሀገር በምግብ ራስን ለመቻል የተጀመረው የማምረት ግብ የሚሳካው ተገቢው ግንዛቤ ሲፈጠር መሆኑን ተናግረዋል።

ኢዜአ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የመሸጋገር ሀገራዊ ግብ ላይ ግንዛቤ በሚፈጥሩ የይዘት ስራዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር አበክሮ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም