ቀጥታ፡

ብልጽግና ፓርቲ የተገበራቸው ሰው ተኮር የልማት ተግባራት ስኬታማ ናቸው - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

አርባ ምንጭ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፦ ብልጽግና ፓርቲ ተግባራዊ ያደረጋቸው ሰው ተኮር የልማት ስራዎች ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ ስኬታማ በመሆናቸው ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ተናገሩ።

የጋሞ ዞንን ወክለው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩ ዕጩዎችን የሚያስተዋውቅ የድጋፍ ሰልፍ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።


 

በመርሃ-ግብሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የአርባ ምንጭ ምርጫ ክልል ዕጩ የሆኑት አቶ ጥላሁን ከበደ ብልጽግና ፓርቲ በየደረጃው የህዝቡን የልማት ጥያቄ እየመለሰ ያለ ሰው ተኮር ፓርቲ ነው ብለዋል።

ፓርቲው ትናንትናና ዛሬ ስራ ላይ ያለ ለነገም ያለ እረፍት እየተጋ የሚቀጥል ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር የሚያሻግር የህዝብ ፓርቲ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ህዝቡ የልማትና የሰላም ባለራዕይ የሆነውን ብልጽግና ፓርቲን በመምረጥ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር በማሻገር ተጠቃሚነቱን ማስቀጠል እንደሚገባውም ነው ጥሪ ያቀረቡት።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በምርጫው ሂደት ህዝቡ የበኩሉን እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፈዋል።


 

የዞኑ ህዝብ ከ2010 ዓ/ም ጀምሮ የብልጽግና ፓርቲ ሁለንተናዊ የልማት ትሩፋቶችን እያጣጣመ ይገኛል ያሉት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ (ዶ/ር) ብልጽግና ፓርቲ በውጤት የታጀበ ፓርቲ ነው ብለዋል።

ፓርቲው ቃልን በተግባር የሚፈጽም በመሆኑ የዞኑ ህዝብ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓም በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲን በመምረጥ የተጀመረው ልማት እንዲጠናከር የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።


 

የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ መስፍን መንዛ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ከተማ አስተዳደሩ ምርጫው በህዝቡ ዘንድ ፍጹም ቅቡልነት ያለውና ሰላማዊ እንዲሆን እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

ፓርቲው የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የሚጨበጥ፣ የሚቆጠርና የሚታዩ ልማቶችን ሠርቶ እያሳየ ያለ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በየአካባቢው እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ብልጽግና ፓርቲን እንዲመርጡም ነው መልዕክት ያስተላለፉት።

በመርሃ-ግብሩ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም