ቀጥታ፡

በጠቅላላ ምርጫው የወጣቶችን ተሳትፎ ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጓል

ጭሮ /ግንቦት 6/2018 (ኢዜአ)፡-በጠቅላላ ምርጫው የወጣቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ወጣቶች ማህበር አስታወቀ።

የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እና ለሀገር መፃኢ ዕድል ቁልፍ መሣሪያ ነው።

በዞኑ ወጣቶች በምርጫው ሂደት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ ሰፊ ቅስቀሳ ተደርጓል።

የወጣቶችን የምርጫ ተሳትፎ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ወጣቶች በታዛቢነት እና በምርጫ አስፈጻሚነት እንዲሳተፉ በማድረግ የዜግነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እየተሰራም ይገኛል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የምዕራብ ሐረርጌ ዞን  ወጣቶች ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ሙርቴሳ መሐመድ እንደገለፁት፤ በጠቅላላ ምርጫው እውን በሚሆነው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የወጣቶችን ተሳትፎ ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጓል።

ወጣቱ  በዕውቀት ላይ ተመስርቶ እንዲመርጥ እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየተሰጠ ነው ብለዋል።

ምርጫ ለሰላምና ለዴሞክራሲ ግንባታ መሰረታዊ ጉዳይ በመሆኑ ወጣቱ በንቃት በመሳተፍ ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ  እንዲጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለዚህም ማህበሩ ግንዛቤ ከመስጠት ባለፈ፣ በዞኑ በሚገኙ 15 ወረዳዎችና 5 ከተሞች ውስጥ ሂደቱን የሚከታተሉ 2 ሺህ 756 የምርጫ ታዛቢዎችን መድቧል ነው ያሉት።

ወጣቱ የአንድ ሰው ድምጽ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያለውን ወሳኝነት በመረዳት በካርዱ የሚበጀውን የፖለቲካ ፓርቲ  በዕውቀት እንዲመርጥም ጥሪ አቅርበዋል።

ከጭሮ ከተማ ወጣቶች መካከል ወጣት አብደላ መሐመድ እና ወጣት መሐመድ ሐሰን በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በከተማው ወጣቶች ማህበር በኩል  በተፈጠረው ግንዛቤ የምርጫ ካርድ በመውሰድ ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል።

በምርጫ ካርዳቸው ለሀገር ግንባታ የተሻለ ሀሳብ ያለውን ፓርቲ ለመምረጥም በመገናኛ ብዙሃን እና በተለያዩ አማራጮች የሚደረጉ የምርጫ ቅስቀሳዎችን እየተከታተሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም