ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል በመኽር እርሻ እስካሁን 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት ታርሷል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ለ2018/19 የምርት ዘመን በመኽር እርሻ ከታቀደው ውስጥ እስካሁን 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት ታርሶ ለዘር መዘጋጀቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ መንግስት በየዓመቱ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለአፈር ዝግጅት፣ ለግብዓት አቅርቦትና ለቴክኖሎጂ አጠቃቀም ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ሀላፊ በሪሶ ፈይሳ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በክልሉ በዘንድሮ የመኽር እርሻ 11 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በማልማት 367 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ለግብርና ዘርፉ በተሰጠው ትኩረት ከአርሶ አደሮች ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የዘርፉ አመራርና ባለሙያ እቅድ በማውጣት በውይይት ተጠናክሮ የማሳ ዝግጅት በከፍተኛ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘር ለመሸፈን ከታቀደው 11 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር መሬት በእስካሁኑ እንቅስቃሴ 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታሩ ታርሶ ለዘር መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

እስካሁን ከታረሰው መሬት ውስጥም አንድ ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑንም አክለዋል።

በክልሉ በአሁኑ ጊዜ የዝናብ ሁኔታው ጥሩ ደረጃ ላይ በመሆኑ በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች በአራቱ የወለጋ ዞኖችና ጅማና ኢሉባቦር ዞኖች ቀድመው የሚደርሱ እንደ በቆሎ፣ በሀረርጌ አካባቢዎች ደግሞ የማሽላ ሰብሎች ዘር መዝራት ተጀምሯል ብለዋል።


 

ከታቀደው ማሳ ከስድስት ሚሊየን ሄክታር መሬት በላይ በትራክተር የሚታረስ መሆኑን አንስተው፣ ልማቱ በኩታ ገጠም እንደሚከናወንም ገልጸዋል።

በክልሉ በቂ የግብዓት አቅርቦት መኖሩን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ጊዜ የአፈር ማዳበሪያ እና 300 ሺህ ኩንታል የሚሆኑ የተለያዩ አይነት ምርጥ ዘሮች በሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች መድረሱን አንስተዋል።

በኦሮሚያ ክልል ዘንድሮ ለአጠቃላይ የግብርና ልማቱ 10 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያና ከሁለት ሚሊየን ኩንታል በላይ የተለያዩ ምርጥ ዘሮች ጥቅም ላይ እንደሚውሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም