አዲስ አበባ የቀዳማይ ልጅነት ልማትን ከከተማ ፕላንና ልማት ጋር በማቀናጀት መተግበሯ በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ የቀዳማይ ልጅነት ልማትን ከከተማ ፕላንና ልማት ጋር በማቀናጀት መተግበሯ በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ የቀዳማይ ልጅነት ልማትን ከከተማ ፕላንና ልማት ጋር በማቀናጀት መተግበሯ በአርዓያነት የሚጠቀስ አስደናቂ ተግባር ነው ሲሉ ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ።
የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻ እና የህፃናት መጫወቻ ስፍራዎች ግንባታ ለሌሎች የዓለም ከተሞች አርዓያ የሚሆኑ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
አዲስ ዓለምአቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ጉባኤ “አፍሪካ በቀዳማይ ልጅነት ሥርዓት ለውጥ የግንባር ቀደምትነት ሚና፤ ከአካባቢያዊ ሞዴሎች ወደ ዓለምአቀፍ እንቅስቃሴ” በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወቃል፡፡
በዚህም ከፅንስ እስከ ስድስት ዓመት የዕድሜ ክልል የሚደረግ ስኬታማ ኢንቨስትመንት አዲስ አበባን የአፍሪካ ተመራጭ የህፃናት ማሳደጊያ ከተማ እያደረጋት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በአዲስ አባባ እየተከናወነ ያለውን የቀዳማይ ልጅነት ልማት በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ተመራማሪዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች፤ ከተማዋ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ከከተማ ፕላንና ልማት ጋር አስተሳስራ እየሰራች ያለችበት መንገድ አስደናቂ ነው፡፡
በፈረንሣይ ሬንስ ዩኒቨርሲቲ የወላጆች አዕምሮ ተመራማሪ ጆዲ ፓውሉስኪ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በአዲስ አበባ እየተተገበሩ ያሉ ፈጣን የልማት ስራዎች የከተማ እድገት ለህፃናት ደህንነትና ለጤና አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮችን እንዴት ማካተት እንዳለበት የሚያሳይ ትልቅ ምሳሌ ናቸው፡፡
ከተማዋ ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢን፣ አረንጓዴ ቦታዎችንና የመጫወቻ ስፍራዎችን በማስፋፋት በኩል ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለችም ብለዋል።
ይህም ለቤተሰቦች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ሌሎች የዓለም ከተሞችም የአዲስ አበባን ተሞክሮ በመቀመር በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
እነዚህ የልማት ስራዎች ለህፃናት እድገትና ለአጠቃላይ ማህበረሰቡ ጤና የሚኖራቸው ሚና እጅግ አስፈላጊ እንደሆነም ነው የጠቆሙት፡፡
የከተማ ፕላኒንግ እና አርክቴክቸር ፕሮፌሰር የሆኑት አሩናቫ ዳስጉፕታ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አዲስ አበባ ለህፃናት ምቹ የሆኑ ስፍራዎችን ለመፍጠር የሚታዩና ተግባራዊ የሆኑ በርካታ አበረታች እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች ብለዋል፡፡
ከተማዋ እያሳየችው ያለው ጠንካራ ቁርጠኝነት እና የተጀመሩ ተነሳሽነቶች አሁኑኑ በግልጽ በስራ እየታዩ መሆናቸው ለሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ትልቅ ተሞክሮ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ተሞክሮ ሌሎች የዓለም ከተሞች በፍጥነት ሊቀስሙት የሚገባ ጠንካራ ምሳሌ መሆኑም ጠቅሰዋል፡፡
በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የህፃናት እድገት ማዕከል ከፍተኛ ባልደረባ የሆኑት ጄምስ ኬርንስ እንዳሉት፤ በአዲስ አበባ የቅድመ ሕፃናት እንክብካቤ ተነሳሽነት ከኮሪደር እና ከአረንጓዴ ልማት ጋር መቀናጀቱ ከተማዋን ለቤተሰብ ምቹ የማድረግ ስትራቴጂ አካል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በከተማው ለሕፃናትና ለቤተሰቦች ደጋፊ የሆነች ከተማን ለመፍጠር በወላጆች አማካሪዎች፣ በሕፃናት ማቆያ ማዕከላትና በመጫወቻ ስፍራዎች ግንባታ ላይ የተመዘገበው እድገት እጅግ አስደናቂ መሆኑ ተናግረዋል፡፡
ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ለልጆች እድገት አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶች በጥሩ ሁኔታ እንዲገነቡ መደረጉ ለከተማዋ የልማት ዕቅድ መጠናከር እንደ ጠንካራ ምሰሶ ተጠቃሽ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡