ለከተማዋ ተጨማሪ ውበትን በማጎናጸፍ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን እየሰጠ የሚገኘው አራዳ ፓርክ - ኢዜአ አማርኛ
ለከተማዋ ተጨማሪ ውበትን በማጎናጸፍ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን እየሰጠ የሚገኘው አራዳ ፓርክ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ የተገነባው አራዳ ፓርክ የቀድሞ ፒያሳ ገጽታን በመቀየር ለከተማዋ ተጨማሪ ውበትን በማጎናጸፍ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን እየሰጠ የሚገኝ ምቹ የመዝናኛ ስፍራ መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ጉብኚዎችና ወጣቶች ገለጹ።
በአዲስ አበባ ከተማ በጥራትና በፍጥነት የተገነቡ ፓርኮች፣ የኮሪደርና የወንዝ ዳር ልማቶች መዲናዋን ዘመናዊና ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ እያደረጓት ይገኛሉ።
አዲሱ አራዳ ፓርክ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሚያዚያ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ከተደረገ ወዲህ በርካታ ጎብኚዎች ስፍራውን እየጎበኙ ይገኛሉ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት በመዲናዋ የተሠሩት የልማት ስራዎች የከተማዋን እድገትና ለውጥ ያረጋገጡ ናቸው ብለዋል።
በአራዳ ፓርክ ጉብኝት ሲያደርጉ ያገኘናቸው አቶ ካሳሁን ሙላት፤ በአዲስ አበባ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች ሕፃናትን፣ አዋቂዎችንና ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ያማከሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህ አስደናቂ ልማት ለአሁኑ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም ዘርፈ-ብዙ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመው ስኬቶቹ የኅብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።
ሌላኛዋ የፓርኩ ጎብኚ ተማሪ ማያ ጆን በበኩሏ፤ በመዲናዋ በመንግሥት የተገነቡ ልዩ ልዩ ፓርኮችን መጎብኘቷን አስታውሳ የአራዳ ፓርክ በዓይነቱ ለየት ያለና ማራኪ ገጽታ የተላበሰ ስፍራ ሆኖ እንዳገኘችው ተናግራለች።
እነዚህ የልማት ሥራዎች የመዲናዋን ገጽታ ከመለወጥ ባለፈ ለወጣቱ ትውልድ ምቹና ብሩህ ተስፋ የምታሰንቅ ከተማ ለመፍጠር ያስችላሉ ስትል ገልጻለች።
ከሐረር ከተማ የመጡትና ፓርኩን ሲጉበኙ ያገኘናቸው አቶ ማሂር ከማል፤ ስፍራው ከጠበቁት በላይ እጅግ አስደናቂ ገጽታ ተላብሶ እንዳገኙት ተናግረዋል።
በተለይም በፓርኩ ውስጥ የተገነቡት ዘመናዊ የእግረኛና የሳይክል መንገዶች፣ ማራኪ መናፈሻዎችና ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ለጎብኚዎች ልዩ እርካታ እንደሚሰጡ አብራርተዋል።
ከልጆቻቸው ጋር በአራዳ ፓርክ ሲዝናኑ ያገኘናቸው አቶ ከማል ሸሞሎ በበኩላቸው፤ መዲናዋ ቀደም ሲል የነበረባትን የመጫወቻ ስፍራ እጥረት በመቅረፍ ለሕፃናት ምቹ አማራጮችን መፍጠር መቻሏን ገልጸዋል።
ይህም ሕፃናት በቂ እና ምቹ የመዝናኛ ስፍራ እንዲያገኙ እና አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ እድገታቸው ተስተካክሎ እንዲያድጉ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።