ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን የበኩላችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን የበኩላችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል
ደደር፤ ግንቦት 6/2018 (ኢዜአ)፡- 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ስኬታማ እንዲሆን የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የደደር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የደደር ከተማ ነዋሪዎች፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ ምርጫው ስኬታማ እንዲሆንና ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከናወን ከሚመለከታቸው የሰላም፣ የቁጥጥርና ሌሎች አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አባገዳ አብዱማሊክ ጁንዲ፤ ምርጫው ነፃና ሰላማዊ ሆኖ እንዲካሄድ የላቀ ድርሻና ኃላፊነት እንዳለባቸው በመገንዘብ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው።
ህዝቡ በምርጫው እንዲሳተፍ ለማድረግ ከሁሉም አካላት ጋር በመቀናጀት መስራታቸውን ጠቁመው፤ መራጩ ህዝብም በድምጽ መስጫ ወቅት ይበጀኛል ለሚለው ፓርቲ ድምጹን እንዲሰጥና ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ምርጫው የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብት ማረጋገጫ ነው ያሉት ደግሞ በደደር ከተማ በንግድ ስራ የሚተዳደሩት አቶ አብዱሹ አህመድ ናቸው።
የመራጮች ምዝገባ መካሄድ ከጀመረበት እለት አንስቶ ህዝቡን የማንቃት ሥራ እየሰሩ መሆኑን አንስተው ምርጫው ያለምንም ችግር ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ የበኩሌን እወጣለው ሲሉም አክለዋል።
ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ አድናን ሻፊ በበኩላቸው፤ የምርጫውን እለት በጉጉት እየጠበቁና በተለይም ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።
ምርጫው ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ እንዲሁም ወጣቶች በንቃት እንዲሳተፉ የበኩላቸውን ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን የጠቆሙት ደግሞ አቶ አብደላ አህመድ ነው።
ለምርጫው ሰላማዊነትና ስኬት በተለይም ወጣቶችን በማስተባበር እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።