ቀጥታ፡

በወሰድነው የመራጭነት ካርድ ለሀገር ልማትና ዕድገት ይበጃል የምንለውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፦ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የወሰዱትን የመራጭነት ካርድ ለሀገር ልማትና ዕድገት ይበጃል ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አስተያየት የሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24/2018ዓ.ም መራጮች ድምፅ ይሰጣሉ።

የዘንድሮው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባም ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 28/2018 ዓ.ም የተከናወነ ሲሆን ሁለት የበዓል ቀናትን ሳይጨምር እስከ ሚያዚያ 14/2018 ዓ.ም በማራዘም ተካሂዶ ተጠናቋል።

በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ድምፅ መስጫ ካርድ ላልወሰዱ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ በዩኒቨርሲቲ ለሚገኙ ተማሪዎችና በካምፕ ለሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በልዩ ሁኔታ እስከ ሚያዝያ 24 ቀን 2018ዓ.ም በማራዘም አጠናቋል።

መራጮች በዲጂታል "ምርጫዬ" መተግበሪያና በየምርጫ ጣቢያዎች በአካል በመገኘት ከ50 ሚሊየን 514 በላይ መራጮች ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ መውሰድ ችለዋል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም 47 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች 10 ሺህ 934 ዕጩዎችን በማስመዝገብ በመገናኛ ብዙኅን አማካኝነት የፖሊሲ አማራጭ ሃሳባቸውን ለህዝብ በማስተዋወቅ ላይ ናቸው።

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለምርጫ ታዛቢነት ዕውቅና የተሰጣቸው 55 የሀገር ውስጥ ድርጅቶችም በተለያዩ አካባቢዎች ከ60ሺህ 277 በላይ ወኪሎችን አሰማርተዋል።

በመራጮች ትምህርት ላይ ዕውቅና የተሰጣቸው 169 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም ለመራጩ ህዝብ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና ስልጠና እየሰጡ ይገኛሉ።

በአዲስ አበባ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመመዝገብ ካርድ የወሰዱ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ ለሀገርና ለሕዝብ ይበጃል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል።

ከመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል ወርቁ ፍቃዱ እንደገለጹት፤ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ካርድ ከማውጣት ጀምሮ የምርጫውን ቀን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ እየሩሳሌም ሀረገወይን በበኩላቸው፤ በምርጫ ካርዳቸው ለሀገር ልማትና ዕድገት ዕውን መሆን ለሚሰራ ፓርቲ ይሁንታ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ሌሊሳ ጋዲሳም እንዲሁ፤ የምርጫ ካርድ በማውጣት ለሀገር ይበጃል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ የድምፅ መስጫ ቀኑን እየተጠባበቁ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል።

የምርጫ ሂደትም ፍትሀዊ፣ ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የመዲናዋ ነዋሪ ወደሬ ገብረጻዲቅ እንደተናገሩት፤ ምርጫ ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ወሳኝ መሆኑን በመጠቆም፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን ዝግጅት አድርገዋል።

አቶ ድሪቢሳ ጥሩነህ በበኩላቸው፤ ምርጫው ሕገ-መንግሥታዊ የመምረጥና መመረጥ ዴሞክራሲያዊ ማረጋገጫ ወሳኝ መድረክ በመሆኑ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሀገር ሰላም፣ ልማትና ዕድገት መረጋገጥ ለሚሰራ ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት ከወዲሁ ተዘጋጅቻለሁ ያሉት ደግሞ አቶ ተሾመ አስፋው ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም