አሶሳ ዩኒቨርሲቲ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች እያሰራጨ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አሶሳ ዩኒቨርሲቲ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች እያሰራጨ ነው
አሶሳ፤ ግንቦት 5/2018(ኢዜአ)፦ ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ያገኟቸው የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎች በእንስሳት እርባታ ስራቸው የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው በአሶሳ ዞን የኡራ ወረዳ አርሶአደሮች ተናገሩ።
የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ማዕከል የተሻሻሉ የፍየል ዝርያዎችን በኡራ ወረዳ ለሚገኙ አርሶአደሮች አሰራጭቷል።
ዩኒቨርሲቲው በረጅም ጊዜ ምርምር ያገኛቸውና ለአርሶ አደሮቹ ያሰራጫቸው ፍየሎች በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ መንታ ግልገሎችን የሚወልዱና በሽታን የሚቋቋሙ መሆናቸውም ተገልጿል።
ፍየሎቹን የተረከቡት የወረዳው አርሶአደሮች ለኢዜአ እንደሚሉት፤ የእንስሳት ዝርያዎቹ በምርታማነታቸውም ሆነ በሽታን በመቋቋም ረገድ ካሏቸው ጠቀሜታ አንጻር የኑሮ ደረጃቸውን ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።
የተሻሻሉ የፍየል ዝርያ ማግኘታቸው የእንስሳት እርባታ ዘርፍን በሳይንሳዊ መንገድ በማከናወን የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸውም ተናግረዋል።
አርሶአደር ዘካሪያ መርሱቅ እና ዘይነብ መኮነን በአሁኑ ወቅት የሚያረቧቸውን ፍየሎች አስፈላጊውን እንክብካቤ እያደረጉላቸው እንደሆነ ገልፀው ከዩኒቨርሲቲው ያገኟቸው ፍየሎች ደግሞ የእንስሳት እርባታ ስራቸውን በተሻለ መልኩ ለመስራት ዕድል እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል።
ለፍየል ዝርያዎቹ አስፈላጊውን ጥበቃ በማድረግና አብዝተው በማርባት ከራሳቸው ባለፈ ለሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ሌላው አርሶአደር ሙሐመድ ሳሌ በበኩላቸው፤ ከዩኒቨርሲቲው ባገኙት የተሻሻለ የፍየል ዝርያ በእንስሳት እርባታ ዘርፍ በስፋት ለመሰማራት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።
የእንስሳት መኖ እና መጠለያ በማዘጋጀት ከወዲሁ በእርባታው ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን እየሰሩ መሆናቸውንም አብራርተዋል።
የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የተሻሻሉ የሰብል እና የእንስሳት ዝርያዎችን ለአርሶአደሩ በማድረስ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ነው ያሉት ደግሞ የኡራ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታጀዲን ሙሐመድ ናቸው።
ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊት በምርምር ያወጣቸው የጤፍ ዝርያ የወረዳውን አርሶአደሮች ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ አሁንም የእንስሳት እርባታ ዘርፍን በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ የጀመረው የምርምር ስራ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
የተሻሻሉ የፍየል ዝርያዎችን የተረከቡ አርሶአደሮች ውጤታማ እንዲሆኑ የወረዳው አስተዳደር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።