በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገር የወጡ የኢትዮጵያ ቅርሶች በዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲመለሱ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገር የወጡ የኢትዮጵያ ቅርሶች በዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲመለሱ እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2018(ኢዜአ)፦ በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገር የወጡ የኢትዮጵያ ቅርሶች በመንግስት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ገለጹ።
በእንግሊዝ ሀገር የነበሩ የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።
ቅርሶቹ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፣ አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) እና ተተኪ አርበኞች አቀባበል አድርገዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገር የተወሰዱና ተዘርፈው የነበሩ የኢትዮጵያ ቅርሶች በመንግስት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲመለሱ እየተደረገ ነው።
በዛሬው እለትም የአፄ ቴዎድሮስ የእጃቸው የወርቅ አምባር፣ የፀጉራቸው ቁንዳላ (ትንሽ ዘለላ) እና የሸማ ሸሚዝ ቁራጭ ቅርሶች ወደ ሀገር ቤት መመለሳቸውን አስረድተዋል።
መንግስት ባደረገው ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረትና በተደረገ ስምምነት ቅርሶቹ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ መደረጉንም ገልጸዋል።
ይህም በኢትዮጵያና በእንግሊዝ ተቋማት ትብብር የተገኘ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።
ቅርሶቹን በተዘጋጀላቸው ሙዚየም በክብር በማስቀመጥ ዜጎች ታሪክና ማንነታቸውን እንዲገነዘቡ ይደረጋል ብለዋል።
በቀጣይም በተለያዩ ምክንያቶች የተወሰዱ ቅርሶችን ለማስመለስ የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።
ማህበራዊ አንትሮፖሎጂስትና ተመራማሪ አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ቅርሶቹ ከአፄ ቴዎድሮስ ጋር ቁርኝት ያላቸው ናቸው ብለዋል።
በእንግሊዝ የኪንግስ ኦን ሮያል ሬጅመንት ሙዚየም ትረስት ሊቀመንበር ሮቢን ጃክሰን (ዶ/ር)፤ ከ150 ዓመታት በኋላ እነዚህን ቅርሶች ወደ ቤታቸው መመለስ መቻሉ ድንቅ አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ በማድረግ ሂደት በነበራቸው እገዛም ትልቅ ኩራት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።