የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከሀዲያ ሆሳዕና መቻል ከነገሌ አርሲ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ - ኢዜአ አማርኛ
የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከሀዲያ ሆሳዕና መቻል ከነገሌ አርሲ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 32ኛ ሳምንት ዛሬ በሚደረጉ አራት ጨዋታዎች ይጀመራል።
ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ሲዳማ ቡና ከሀዲያ ሆሳዕና በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሲዳማ ቡና በ55 ነጥብ አንደኛ ደረጃን ይዟል። ሀዲያ ሆሳዕና በ38 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ከድል የራቀው ሲዳማ ቡና ወደ አሸናፊነት ለመመለስ እና መሪነቱን ለማጠናከር ይፋለማል።
በ31ኛ ሳምንት ሃዋሳ ከተማን 1 ለ 0 የረታው ሀዲያ ሆሳዕና ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ መቻል ከነገሌ አርሲ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታም ትኩረት ስቧል።
መቻል በ49 ነጥብ ሶስተኛ፣ ነገሌ አርሲ በ51 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አቻ የወጣው መቻል ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባል።
ተጋጣሚው ነገሌ አርሲ ተከታታይ የሊግ ድሎችን ያስመዘገበ ሲሆን ሶስት ነጥብ በዋንጫ ፉክክሩ እንዲቆይ ያደርገዋል።
በሊጉ አናት ላይ የሚገኙ ክለቦች የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በዋንጫ ፉክክሩ ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ናቸው።
ወላይታ ድቻ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ያሸነፈው ወላይታ ድቻ በ41 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ39 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ በ31ኛ ሳምንት መቀሌ 70 እንደርታን 1 ለ 0 አሸንፏል።
ሁለቱ ቡድኖች በድል ጉዟቸው ለመቀጠል የሚያደርጉት ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ምድረ ገነት ሽሬ ከኢትዮጵያ ቡና በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ምድረ ገነት ሽሬ በ33 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ኢትዮጵያ ቡና በ43 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በ31ኛ ሳምንት በአዳማ ከተማ የ4 ለ 0 ሽንፈት ያስተናገደው ምድረገነት ሽሬ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።
ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም። ሁለቱም የአሸናፊነት መንገድን ለማግኘት ይጫወታሉ።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 32ኛ ሳምንት እስከ ግንቦት 8 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
አቤል ያለው ከሲዳማ ቡና የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን በ14 ጎሎች እየመራ ነው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫዋቾች የሆኑት አዲስ ግደይ እና ናትናኤል ዳንኤል በተመሳሳይ 10 ግቦች ይከተላሉ።