በኦሮሚያ ክልል ህገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውርን የመከላከል ስራው በትኩረት እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ህገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውርን የመከላከል ስራው በትኩረት እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፣ግንቦት 6/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ህገወጥ የነዳጅ ዝውውርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ግብይትና አቅርቦቱን ስርዓት የማስያዝ ተግባር በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ህገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ቅንጅታዊ አሰራሩ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ነው ቢሮው አክሎ ያስታወቀው።
በመካከለኛው ምስራቅ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በነዳጅ አቅርቦት ላይ የሚታየውን ዓለም አቀፋዊ ጫና ለመቋቋም መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በኦሮሚያ ክልል ሰፊ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
በቢሮው የንግድ ኢንስፔክሽንና ሬጉላቶሪ ዳይሬክተር አቶ ዲናኦል ደረጀ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በህዝብ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጫና ለመቀነስ የነዳጅ ግብይትና አቅርቦቱን ስርዓት የማስያዝ ስራ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
በክልሉ የነዳጅ አቅርቦቱ ለታለመለት የልማት ግብ እንዲውል ለማድረግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ለትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶች፣ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች፣ ለግብርና ምርቶች ማመላለሻና ለሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ቅድሚያ በመስጠት የማስተናገድ ተግባሩ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
በክልሉ የነዳጅ ስርጭትና ግብይቱን በስርዓት ለመምራት የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ-ኃይል ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን አቶ ዲናኦል ገልጸዋል።
በዚህም ከአስተዳደር፣ ከፖሊስ፣ ከዐቃቤ ሕግ፣ ከንግድና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ግብረ-ኃይል ህገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውርን ለመቆጣጠርና የንግድ ስርዓቱን ለማሳለጥ እያከናወነ ያለው ተግባር ውጤታማ መሆኑን አስረድተዋል።
ግብረ-ኃይሉ አጋጣሚዎችን በመጠቀም በህገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውር ላይ የተሰማሩ አካላትን በመከታተል ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ በህገ-ወጥ መንገድ ከማደያ ውጭ ተከማችቶ የተገኘ ከ558 ሺህ 313 ሊትር በላይ ነዳጅ በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን አስታውቀዋል።
በቁጥጥር ስር የዋለው ይኸው የነዳጅ ምርት በገንዘብ ሲሰላ ግምቱ 85 ሚሊዮን 846 ሺህ 847 ብር ለመንግስት ገቢ መሆኑን አብራርተዋል።
ከህገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውሩ ጋር በተያያዘም 256 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በሕግ ሲታይ መቆየቱን ጠቁመዋል።
ከእነዚህም መካከል እስካሁን 149 ግለሰቦች እስከ 7 ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ መደረጉን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በተከናወኑ የተቀናጁ የቁጥጥር ስራዎችና በተወሰዱ እርምጃዎች በክልሉ የነዳጅ አቅርቦቱ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።
ተግባሩን አጠናክሮ በማስቀጠል ረገድ ነዳጁ ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲውል በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
ህብረተሰቡ በነዳጅ ዝውውር ላይ የሚስተዋሉ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን እንዲሁም በግብርና ምርቶች ላይ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን በመጠቆም የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባም ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።