ኢትዮጵያ የባለብዙ ወገን ግንኙነት እና ዓለም አቀፍ ትብብር ተምሳሌት ናት - የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የባለብዙ ወገን ግንኙነት እና ዓለም አቀፍ ትብብር ተምሳሌት ናት - የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2018 (ኢዜአ)፦ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ትብብርና ለባለብዙ ወገን ግንኙነት ያላትን ቁርጠኝነትና ተምሳሌትነት አደነቁ።
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስምንት አስርት ዓመታት ጉዞን ምክንያት በማድረግ፣ "በሰላም አብሮ ለመኖር" በሚል መሪ ቃል ልዩ የመታሰቢያ ቴምብር ስብስብ አውጥታለች።
የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሁነቱን በማዘጋጀታቸውና የኢትዮጵያ ህዝብ ላደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል።
ልዩ የመታሰቢያ ቴምብሩ ለተመድ 80ኛ ዓመት ምስረታ ከመዘከር ባለፈ ተመድ እና ኢትዮጵያ ያላቸውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1945 ተመድ በሳን ፍራንሲስኮ ሲመሰረት ቻርተሩን ከፈረሙ 51 ሀገራት መካከል አንዷ እንደሆነች አውስተዋል።
ኢትዮጵያ አሁን የባለብዙ ወገን እና ዓለም አቀፍ ትብብር ተምሳሌት ሆና መቀጠሏን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ጥንታዊ ስልጣኔን የምትወክል ሀገር ናት ያሉት ዋና ፀሐፊው በዓለም ላይ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗንም አንስተዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ጠንካራ የታሪክ መሰረት ያላቸው ሀገራት መጻኢ ጊዜያቸው ጠንካራ እና ብሩህ እንደሆነ ገልጸዋል።
አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ገዢዎች ስር በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያ ነጻነቷን አስጠብቃ የቆየች ሀገር መሆኗን ገልጸው ይህም የጥንታዊ ስልጣኔዋ ውጤት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጡ በኋላ የተመድ አባል ሀገራት እንዲሆኑ ድጋፍ ማድረጓንም አስታውሰዋል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀማጫ በአፍሪካ የተመድ ከፍተኛ የተቋማት እና የሰራተኞች ብዛት ከያዙ ከተሞች መካከል እንደምትጠቀስም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች በተመድ ጥላ ስር በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ወሳኝ ሚና መጫወታቸውን አንስተውም በዓለም ላይ አደገኛና አስጊ የሚባሉ ቦታዎች በመሄድ መስዋዕትነት በመክፈል ሰላም እና መረጋጋት ለተወጡት ሚና ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ተመድ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ መከባበር መርህ ትብበሩን ማጠናከር እንደሚሻና አጋርነቱን ለማጎልበት ቁርጠኛ መሆኑን አመልክተዋል።
የተመድ ግብ የኢትዮጵያ ህዝብ ማገልገል እና የኢትዮጵያ መንግስት ስትራቴጂዎች እንዲሳኩ መደገፍ ነው ብለዋል።
ተመድ ለኢትዮጵያ በሰላምና ደህንነት፣ በልማት፣ በሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት እና የተቋማት አቅም ግንባታ ላይ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ተመድ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፍትሐዊ የዓለም አስተዳር ስርዓት እንዲሰፍን ያላቸውን ጥሪ እንደሚደግፍና ለስኬታማነቱም እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ በማድረግ አሁናዊ የዓለም ሁኔታ እንዲያንጸባርቅ እና በአፍሪካ ላይ የደረሱ ታሪካዊ ኢፍትሃዊነቶች መካስ አለባቸው ብለዋል።
አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና እንታገኝ በማድረግ የምክር ቤት ቅቡልነት እና ውጤታማነት ማሳደግ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጡም አንስተዋል።
አፍሪካ የቅኝ ግዛት እና በዓለም ተቋማት ፍትሃዊ በሆነ ሁኔታ ያለመወከሏ ሁለት ጉዳት መሆኑን ያነሱት ዋና ፀሐፊው ኢትዮጵያ ከተመድ መነሻው የአፍሪካ ተወካይ መሆኗን አድንቀዋል።
ተመድ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሬፎርም እና የአፍሪካ የጸጥታው ምክር ቤት ውክልና እንድታገኝ ያቀረበችው ጥሪ ተገቢና ድርጅቱ ፍላጎቱ እውን እንዲሆን ይሰራል ብለዋል።
አፍሪካ በዓለም የፋይናንስ ስርዓት ውስጥ ፍትሐዊ ተጠቃሚ መሆን እንዳለባትና ውሳኔ ሰጪነቷ ሊያድግ እንደሚገባ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ያሳተመችው ልዩ የመታሰቢያ ቴምብር ተመድ እስከ አሁን የመጣበትን የሚያወሳ ከመሆን ባለፈ አሁን ዓለም ላይ የታጋረጡ ፈተናዎችን በጋራ መፍታት እንዳለብን የሚያሳስብ ነው ብለዋል።
ሰላም፣ ፍትህ እና ብልጽግና ለሁሉም የሚለው የተመድ የጸና እሳቤ ትርጉም ያለው እና የማይተካ መሆኑን አንስተዋል።
ለተሻለች አፍሪካ እና ዓለም መፈጠር በጋራ እንስራ ሲሉ ጥሪ ያቀረቡት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን እንድትወጣ ጥሪ አቅርበዋል።