ቀጥታ፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፍትሐዊነት እና የዓለምን አሁናዊ ሁኔታ ያማከለ ለውጥ ያስፈልገዋል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2018 (ኢዜአ)፦ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፍትሐዊ፣ አካታች እና የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ ያማከለ ለውጥ እንደሚያስፈልገው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የስምንት አስርት ዓመታት ጉዞን ምክንያት በማድረግ፣ "በሰላም አብሮ ለመኖር" በሚል መሪ ቃል ልዩ የመታሰቢያ ቴምብር ስብስብ አውጥታለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 80ኛ ዓመት በሚከበርበት ወቅት የባለብዙ ወገን ተቋማት እየተለወጠች ካለው ዓለም ጋር አብረው መጓዝ እንዳለባቸው አጽንኦት መስጠት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ከ80 ዓመታት በፊት ከአስከፊው ጦርነት በኋላ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መቋቋሙን አውስተዋል።

የተመድ መቋቋም ሀገራት በጋራ መርህ ለሰላም፣ ክብር እና መረጋጋት በትብብር መስራት አለባቸው ከሚለው እሳቤ የመነጨ መሆኑን አመልክተዋል።

ይህ እሳቤ በተመድ ቻርተር ውስጥ መካተቱን ጠቅሰው ለሰብዓዊ ክብር፣ ፍትህ፣ እኩልነት እና ማህበራዊ ለውጥ የቻርተሩ ምሰሶዎች እንደሆኑ ነው ያነሱት።


 

ኢትዮጵያ ከተመድ መስራች ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዓለም አቀፍ ስርዓት ውስጥ ያላት ታሪክ በመርሕ የተመሰረተ እና ከፍተኛ ፈተናን ያለፈ መሆኑን አመልክተዋል።

የጋራ ደህንነት እሳቤ ውጤታማ ባልሆነበት የሊግ ኦፍ ኔሽን ውድቀት ኢትዮጵያ በወቅቱ መመልከቷን ጠቅሰው፤ ያ ታሪክ ኢትዮጵያ ለትብብር ጀርባውን እንዳትሰጥ ማድረጉን ነው ያነሱት።

ኢትዮጵያ በወቅቱ ከነበረው ሁነት ትምህርት መውሰዷንና የተቋማት ተአማኒነት የሚለካው በፈተና ወቅት በሚሰጠው ምላሽ መሆኑን የጸና አቋም መያዟን ተናግረዋል።

በሀገራት መካከል ያለ መተማመን ጫና ውስጥ ገብቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግጭቶች ይበልጥ እየተወሳሰቡ መምጣታቸውን አንስተዋል።

በቃል ኪዳኖች እና በትበራዎች መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መምጣቱንም አስረድተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሁናዊ የዓለም ሁኔታን ያማከለ፣ ፍትሃዊ እና አካታች በሆነ መልኩ ራሱን እየለወጠ መሄድ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።


 

አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅ እና በዓለም አቀፍ ስርዓት ውስጥ ውክልና ማግኘት እንዳለባት እና አፍሪካ በታላቅ ኃላፊነት የበኩሏን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ ናት ብለዋል።

አፍሪካ ጠንካራ እና ይበልጥ ተአማኒነት ያለው የዓለም ስርዓት እንዲገነባ አበክራ እንደምትሰራም ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሰላም እና ደህንነት፣ ልማት፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና ፈጣን የቴክኖሎጂ እድገት ምላሽ መስጠት እንዳለበት አመልክተዋል።

እነዚህ ፈተናዎች ምላሽ እንዲያገኙ ጥልቅ ትብብር፣ ጠንካራ አጋርነት እና ትርጉም ያለው ዓለም አቀፍ ትብብር እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከፊታችን ያለው ኃላፊነት ግልጽ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዓለም የባለብዙ ወገን ስርዓት ጊዜውን የሚመጥን ለውጥ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እና ለቡድናቸው፣ ሰላምን፣ ልማትን እና ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር እያሳዩት ላለው ጽኑ አመራር አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ዋና ጸሐፊው ተመድን ከአፍሪካ ጋር ያለው ትብብር እንዲጠናከር እያከናወነ ላለው ስራ አፍሪካውያን ትልቅ ዋጋ ይሰጣሉ ብለዋል።

ዛሬ ኢትዮጵያ ይፋ ያደረጋቻቸው ታሪካዊ ቴምብሮች ለተመድ እሳቤዎች ትግበራ ለተጉ በሙሉ እውቅና የሚሰጡ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የባለብዙ ወገን ትብብር ፍትሃዊ፣ አካታች እና ውጤት ተኮር መሆን እንዳለበት በጽኑ ታምናለች፣ ለዚህ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም መጻኢ ሁኔታ የበኩሏን ሚና እንደምትወጣ ገልጸው አሁን ባለንበት ዓለም ትብብር ለሰላምና መረጋጋት ቁልፍ ምሰሶ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም